የባዘርኔት ፕሮጀክትን በውጤታማነት ለመተግበር የስትሪንግ እና ቴክኒክ ኮሚቴ ድርሻቸው የላቀ ነው ተባለ።
አዳማ፡ መስከረም 22/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለውን ውይይት ከስትሪንግና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ጋር አካሂዷል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ውጤታማ ስራ ለመስራት የስትሪንግና ቴክኒክ ኮሚቴ ጅርሻ የጎላ ነው ሲሉ በውይይቱ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል።
የውይይቱ ዋና አላማም በባዘርኔት ፕሮጀክት በአዋሽና ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ በጋራ የምናከናውናቸውን ስራዎች በጋራ በመገምገም የጋራ ግንዛቤ ይዘን ለቀጣይ ለምንሰራው ስራ ያለውን አበርክቶ ለማየት ነው ብለዋል።
ስራው ከፌደራል ጀምሮ እሰከ ቀበሌ ባለው መዋቅር የውሃና ኢነርጂ፣ ግብርናና አካባቢ ጥበቃ ሌሎችም ተቋማት በቅንጅት ውጤታማ ስራ ሰርተን በቀጣይ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማምጣት ማሳያ በሚሆን መልኩ በቅንጅት መተግበር ይጠበቅብናል ብለዋል።
የከርሰምድር ውሃ ሀብት የወንዝ ፍሰትና ጥራት በሙሉ የሚከናወኑት መሬት ላይ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ በክልል፣ በዞንና ወረዳ ደረጃ ዝቅ ሲልም ቀበሌ ላይ የምንተገብራቸው ስራዎች ተደምረው ለሀገር በረከት ስለሚያመጡ ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት ቅንጅታዊ አሰራራችን አጠናክረን በመቀጠል የልማቱ ተቋዳሽ መሆን እንችላለን ብለዋል።
የስትሪንግና ቴክኒክ ኮሚቴዎች ድርሻቸው የላቀ መሆኑን አውቀው ለተግባራዊነቱ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ሲሉም ክቡር ሚኒስትሩ አደራ ብለዋል።
በመጨረሻም ፕሮጀክቱን አስመልክቶ የሚቀርቡ ጽሁፎችን በሚገባ በመከታተል ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችንና አስተያየቶችን በመስጠት በጋራ የምንተገብረውን ፕሮጀክት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ማድረግ እንችላለን ስሉም ክቡር ሚኒስትሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ መዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተሠጠው ተግባርና ሀላፊነት መሰረት በሶስት ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ጠቅሰው ተፋሰስን መሠረት አድርገው የሚሰሩ ሰራዎች ዘላቂና ውጤታማ ናቸው ብለዋል።
የውይይቱ ዓላማም የባዘርኔት ፕሮጀክት በሁለቱ ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ ሲደረግ በዋናነት በክልሎች ተግባራዊ እንደመደረጉ በየደረጃው ያለው አካል ድርሻው ምን እንደሆነ በማየት እና በመናበብ ውጤታማ ስራ ለመስራት ታላሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ብዙነህ አስፋው የፕሮግራሙን ዓላማና ግብ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ያሉ ጉዳይች እና የቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝነትን እና ተያያዠ ጉዳዮችን በዝርዝር አቅርበዋል።
የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሞላ ረዳ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ጋር በቅንጅት እንዴት እንደሚሰራ፣ ከጣሊያን መንግስት በተገኘ የ31.5 ሚሊየን ዮሮ በጣም ገጠራማ የሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮችን የንሮ ደረጃ ለማሻሻል እንደሚሰራና የስትሪግና ቴክኒክ ኮሚቴ ተግባርና ሀላፊነትም ምን እነደሆነ በዝርዝር አቅርበዋል።
በተጨማሪም የአዋሽ ተፋሰስ የባዘርኔት ፕሮጀክት አተገባበር ምን እንደሚመስል ዮሀንስ ዘሪሁን እንዲሁም የባዘርኔት ፕሮጀክት አተገባበር በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ምን እንደሚመስል ደግሞ በአቶ አቢቲ ጌታነህ ቀርበው በርካታ፣ ሀሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተንጸባርቀዋል።
በተነሱ ሀሳቦች፣ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎች እና ወደፊት መሻሻል በሚገባቸው እና በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ጉዳዮችም ጭምር ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ግልጽ የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተውባቸዋል ።