ኢትዮጵየውያን በራሳችን የገንዘብ አቅም አይቻልም የተባለውን የህዳሴ ግድብ ገንብተን ያጠናቀቅንበት ዳግም አድዋችን ነው።
ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ
ጳጉሜ 4/2017ዓ.ም ''የማንሰራራት ቀን" የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ።
በእለቱ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ እለቱ ለኢትዮጵያውያን የአይቻልምን መንፈስ ሰብረን በራሳችን አቅም ዳግም አድዋ የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብን ያጠናቀቅንበት ድላችን በመሆኑ ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን ታላቅ በዓል ሲያከብር ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ተጨባጭ ውጤቶች ባስመዘገበባቸው የውሃ ሀብት አስተዳደር፣በመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ሳኒቴሽን እንዲሁም በኢነርጂ ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ ስራዎችን ለማስቀጠል ቃል የምንገባበት ነው ብለዋል።
አክለውም የሀገሪቱን የውሃ ሀብት ለዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማዋል እንዲቻል የውሃ ፖሊሲ በመከለስ ፣ አዋጆችንና ደንቦችን በማርቀቅ የተሳለጠ የውሃ ሀብት አስተዳደር ለመገንባት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ከሀይል አቅርቦት አንጻርም የኢነርጂ ፖሊሲ በመከለስ በግሪድና በኦፍ ግሪድ ቴክኖሎጅ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ ማድረግ መቻሉንና በሀይል አቅርቦቱም ሆነ በሀይል ሽያጭ ባለፉት አራት ዓመታት ከፍተኛ እምርታ ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢዮጵያን የብልጽግና ጎዳና ለማረጋገጥ ፈር ቀዳጅ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያውያን ብዝሃነታችን አጉልተን በአንድ ተባብረን ብሔራዊ ጥቅማችን ለማረጋገጥ ምንም የሚያግደን ነገር እንደሌለ እንዲሁም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት እንደምንችል ያሳየንበት ትልቅ ድላችን ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም እንደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ማንሰራራት በሚዳሰስ መልኩ እያረጋገጥ መሆኑን ማሳያችንም ነው ብለዋል፡፡
የበዓሉን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮችና የሴክተሮች ክትትል ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አክሊሉ ታደሰ ባለፉት 14 ዓመታት የኢትዮጵያን የድህነት ጉዞ የሚገታ የላብም የደምም እንባ የተከፈለበት ፣ በርካታ ፈተናዎችን ያስተናገድንበት ይህንንም በጽናት አልፈን ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር መሆኗን በተግባር በተከፈለው ደምና እንባ አረጋግጠን ያሳየንበት ሁለተኛው አድዋችን ነው ብለዋል፡፡
ታሪክ የሚሰራ ትውልድ ሲፈጠር አገር ወደ ላይ እያደገች ትሄዳለች ያሉት ክቡር አቶ አክሊሉ አያት ቅድመ አያቶቻችን ያኖሩልንን የአይበገሬነት በጎ ተግባር በማስቀጠል ትውልዱ ከመሪው ጎን በመቆም የተጀመረውን የእድገትና የብልጽግና ጎዳና የማስቀጠል ትልቅ ሃላፊነትን መወጣት እደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
አክለውም የኢትዮጵያ ገናናነት በነበረ የሚወሳ መሆን ከጀመረ የቆየ ቢሆንም የባህር በር ማንም የወሰደብን ሳይኖር በራሳችን የሠጠነው እና ሀገራችን የበለጸገች የመሆን እድሏን አሳጥተን የድህነት መንገድ የመረጥነው እኛው በመሆናችን የባህር በር የማግኘት እጣ ፈንታችንም በራሳችን የሚወሰን እና የመጠቀም መብታችንም በመሆኑ የቀጣዩ የቤት ስራችን ሊሆን ይገባል ብለዋል፡