ጥራት ያለው የግዥና የኮንትራት አስተዳደር ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ ነው።

ጥራት ያለው የግዥና የኮንትራት አስተዳደር ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ ነው። አዳማ፡- ሰኔ 24/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክትን /Basin Scale Resilience intiative for Ethiopia/ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚያስችሉ ተግባራት መካከል የግዥና የኮንትራት አስተዳደር ስራ በመሆኑ ጥራት ያለው የግዥና የኮንትራት አስተዳደር ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ ነው ተባለ። የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉን ከሚደግፉና አጋዥ ከሆኑ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የባዘርኔት ፕሮጀክት የባለሙያውን አቅም በመገንባት፤ በመስኩም የመፈፀም አቅምን ለማሳደግና ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ ባለፈው ሳምንት በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱንም አስታውሰዋል። ስልጠናውን የሚሰጡት የሜክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር እንዳለ መኮንን በኩላቸው ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅም ወደ ትግበራ በሚገባበት ጊዜ ስልጠናው መሰጠቱ ብቁ የሆኑ ሙያተኞች ለማፍራት ያግዛል ብለዋል። ፕሮጀክቱ የግዥና ኮንትራት አስተዳደር በጋራ ታቅዶ የሚተገበር ነው ያሉት ኢ/ር እንዳለ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከአለምአቀፍ አቅራቢዎች ጋር የሚገናኝ በመሆኑ አለምአቀፍ የፕሮጀክት ግዥና ኮንትራት አስተዳደር የክፍያ ስርዓት ምን እንደሚመስል ጥሩ ግንዛቤ አግኝተው ፈጣን፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን እንዲተገብሩ ያግዛል፤ ሰልጣኞቹ ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ ተፈትነው ዕውቅና ይሰጣቸዋልም ብለዋል። ከኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶአደር ልማት ቢሮ የግዥ ዳይሬክተር ወ/ሮ ደመቀች ገ/ጊዮርጊስ እና ከአፋር ክልል ከእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የግዥ ባለሙያ አቶ ሰኢድ ይማም የግዥ አስተዳደር የፕሮጀክት ማስፈፀሚያ አንዱ የስራ አካል በመሆኑ፤ ስልጠናው ለስራችን አጋዥ ግብዓት ከማግኘታችንም በተጨማሪ የሌሎች ተቋማትን ልምድ ያገኘንበት ነው ብለዋል። ሰልጣኞቹ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ስልጠናውን ስላመቻቸ አመስግነው፤ የስልጠናው ጊዜ ወቅቱን የጠበቀና ሌሎች የግዥ ባለሙያዎችንም የሚያሳትፍ ቢሆን ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል። ስልጠናው ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለግዥና ኮንትራት አስተዳደር ባለሙያዎች፣ ለኦሮሚያ፣ ለአፋርና ለሱማሌ ክልል ከውሃ፣ ከግብርና ልማትና አርብቶአደር እና ከግብርና ቢሮ ለግዥና ለኮንትራት አስተዳደር ባለሙያዎች ለተከታታይ አራት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን የግዥ ዕቅድ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ዕቅድን እንዴት መሬት ማውረድና ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል፤ በተለምዶ ሲሰራበት የነበረውን የግዥ ዕቅድ የአሰራር ስርዓት ላይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችንና የነበሩ ብዥታዎችን ለማጥራት እንዲሁም የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል።

Share this Post