ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክብርት አለሚቱ ኡሞድ ጋር ተወያዩ።
ሰኔ18/09/2016 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክብርት አለማቱ ኡሞድ ጋር በአማራጭ ኢነርጂ እና ሌሎች ተያያዥ የልማት ስራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ክብርት አለሚቱ ኡሞድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ክልሉ ያለበትን የሀይል ችግር ተረድቶ በተለይም ከዋናው የሀይል መስመር ርቀው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሀይል ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ የሚያስመሰግን መሆኑ በቅርቡ ለአገልግሎት የሚበቃው የመታር ሶላር ፕሮጀክት ማሳያ ነው ብለዋል።
ክብርት ርዕሰ መስተዳድሯ በማከል በክልሉ ቡና፣ አትክልት እና ፍራፍሬ የሚያመርቱ አካባቢዎች የሶላር ሀይል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን ቢችሉ እና አስፈላጊው መሠረተ ልማት ቢመቻችላቸው ምርታቸው ሳይበላሽ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ የበለጠ ጥሩ ይሆናልም ብለዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ያለውን የመብራት መቆራረጥ ፣የውሃና የመብራት የክፍያ ስርዓትን በተመለከተ እንዲሁም የውሃ ሀብት በደለል እየተጎዳ በመሆኑ የውሃ አካላት ዳርቻ ጥበቃ ስራ እንዲሰራ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መብራት ሀይል አገልግሎት የክልሉን ህብረተሰብ የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ያለው ስራ የሚመሠገን ነው ያሉት ክብርት ርዕሰ መስተዳድሯ በኮሪደር ልማት ምክንያት ለሚከሰት የመብራት መቆራረጥም ድጋፍ እንደሚሹ ጠይቀዋል።
ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህብረተሰቡን የሀይል ተደራሽነት ለማስፋት ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቁመው በዚሁ ክልልም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ የሶላር ግሪዶችን እንየገነባ ሲሆን የሶስት ወረዳዎች የሶላር ሚኒ ግርድ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ገልጸዋል።
በውይይቱ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ አመራሮች ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሀላፊና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።