በአዋሽ ወንዝና በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ዙሪያ በዘንድሮ በጀት ዓመት በተጀመሩ የጎርፍ መከላከል ስራዎች ላይ ክቡር ሚኒስቴሩ በተገኙበት ከአማካሪዎችና ከተቋራጮች ጋር ውይይት ተካሄደ።
ሰኔ 16/2017 ዓ. ም (ው. ኢ.ሚ) በዘንድሮ በጀት ዓመት በአዋሽ ወንዝና በስምጥ ሸለቆ ሀይቆ በተጀመሩት የጎርፍ መከላከል ስራዎች ክቡር ሚኒስቴሩ በተገኙበት ከአማካሪዎችና ከተቋራጮች ጋሪ በአተገባበሩ ላይ ውይይት ተካሄደ።
የጎርፍ መከላከል ስራው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያን መሰረት አድርጎ በተለዩ በሁለቱ ተፋሰሶች በአስር ሎቶች (10 Lots) ማለትም፤ በአዋሽ ወንዝ (በላይኛው፣ በመካከለኛውና በታችኛው አዋሽ) አምስት እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች (በአርባ ምንጭ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ አከባቢ) አምስት ስፍራዎች ላይ አሁን ላይ ስራው ምን ደረጃ ላይ እንዳለ በኢትዮጵያ ግርፍ መከላከል ፕሮጀክትና በአማካሪዎች በኩል ጠቅለል ያለ ጽሁፍ ቀርቧል።
በቀረበው ጽሁፍ ላይም ተቋራጮች ያለውን ምቹ ሁኔታና ተግዳሮቶች አንስተዋል።
በቀረቡት በነጥቦች ላይ በተደረገ ውይይትም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በአንዳንድ ቦታዎች ትኩረት መደረግ እንዳለበት አንስተው፤ በተለይ እስካሁን ያለው አፈጻጸም አጥጋቢ ባለመሆኑ ስራው ከመደበኛ ስራ በተለየ አቀራረብ መሰራት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
አያይዘውም ለስራው ልዩ ትኩረት መስጠት ፣ የዲዛይን ችግር ሲኖር መፍትሔ ማስቀመጥ ፣ በተቋራጮችም ሆነ በአማካሪዎች በኩል ብቃት ያለው የሰው ሀይል ማሰማራት፤ እንዲሁም ለአከባቢና ለማህበረሰብ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከስራው አንገብጋቢነት የተነሳ ከመደበኛ ሰዓት ውጪ ትርፍ ጊዜን መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል። የነዳጅ ችግርም እንዳይፈጠር ቅድሚያ ለዚህ ስራ እንድሰጥ የድጋፍ ደብዳቤ ለክልሎች እንደተጻፈና በማንኛውም ጊዜ እገዛ እንደሚደረግ ገልጸውላቸዋል።
ባጠቃላይ አግባብ ያልሆኑ ምክንያቶችን ሳንፈጥር ችግሮቹን በየደረጃው በፍጥነት በመፍታት ተጠያቂነት ወስደን ህብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጎርፍ ስጋት መቅረፍ አለብን ብለዋል።
በመጨረሻም ስራውን በቦታው በመገኘት ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡