በኢትዮጵያ የገጸ ምድር ውሃ አካላት ጥበቃ፣ ማገገሚያ እና የመልሶ ማቋቋም ረቂቅ መመሪያ ላይ ምክክር እየተደረገ ነው።
ሰኔ 10/2017 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገጸ ምድር ውሃ አካላት ጥበቃ፣ ማገገሚያ እና የመልሶ ማቋቋም
ረቂቅ መመሪያ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እያደረገ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ የውሃ ግኝትን አስተማማኝ ከማድረግ አንጻር እጅግ አሰፈላጊ የሆነውን የውሃ አካላት ጥበቃና መልሶ ማከም ስራዎችን ለማገዝ የሚያስችል የውሃ አካላት ጥበቃ ጋድላይን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጂ.አይ.ዜድ ኔቸርስ ጋር በጋራ ተዘጋጅቶ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡
ጋይድ ላይኑ በውሃ አካላት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመለየት፤ የጥበቃ ሰልቶችን ለመቅረጽ፣ የመልሶ ማገገም ስራዎችን ለመወሰን እና ለውሃ አካላት ደህንነት ጥበቃ ሊኖረው የሚገባውን የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ድርሻ ለማሳወቅ የሚኖረው ሚና የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አክለውም በቅርቡ ከጸደቀው የውሃ አካት ዳርቻ አስተዳደር አዋጅ ጋር በተናበበ አግባብ በሚከለሉ የውሃ አካላት ዳርቻዎች ሊኖር የሚገባውን የስነ-ምህዳር ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎችን ለመለየትና ለማስፈጸም የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመርሀ ግብሩ በዋናነት በረቂቁ አስፈላጊነት የኢትዮጵያ የውሃ አካላት ከብክለት፣ ከአቅም በላይ አጠቃቀም እና ደካማ የመሬት አጠቃቀም፣ከውሃ አያያዝ ሀገራዊ መመሪያ ፣ የአጋር እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እያደገ መሆኑ እንዲሁም በሁሉም ዘርፎች ተሳታፊዎችን አንድ የማድረግ አቅም ለመፍጠር፣ የተዋሃደ መመሪያ የመረጃ አጠቃቀምን እንደሚያሻሽል ፣ ከአለም አቀፍ ግቦች ጋር ይጣጣማል ፣ ፍትሃዊ፣ ዘላቂ የውሃ አያያዝን ለማበረታታል እንደሚጠቅም በዝርዝር ተብራርቷል።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በሀገር ደረጃ ከወሰዳቸው የውጤት መለከያዎች ውስጥ የውሃ አካላት ደህንነትን ማረጋገጥ አንዱና ዋናው በመሆኑ በተለይም በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ አሻራ ልማት ከምትሰጠው ትኩረትና ጥረት አንጻር ይህ ጋይድላይን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉም በዚህ ረገድ የተፋሰስ እቅድን መሰረት በማድረግ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማትን፤ የውሃ አካላት ደህንነት ጥበቃን፣ የውሃ ጥራት ክትትልንና የአረንጓዴ አሻራ ስራን በማስተሳሰር እና በማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መስራት እንደሚጠበቅም ከመድረኩ ተገልጿል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ባለድርሻ አካላት፣ አጋር ድርጂቶች እና የክልል ውሃ ቢሮ አመራርና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።