በኢትዮጵያ የውሃና ሳኒቴሽን ባለድርሻ አካላትን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ነወ።
ሰኔ 2/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የኢትዮጵያ ከተሞች የውሃና ሳኒቴሽን ፌደሬሽን ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የውሃና ሳኒቴሽን ባለድርሻ አካላትን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና በአዳማ እየተሰጠ ነወ።
በስልጠናው መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ታምሩ ገደፋ ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ ከአቅም ግንባታ ጋር በተያያዘ ለ18 ከተሞች ድጋፍ ማድረጉን እና ለሶስት ከተሞች ደግሞ በልዩ ሁኔታ አቅማቸውን የመገንባት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
የስልጠናው ዋና አላማም የመማማር ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ የውሃ አገልግሎቶች በስታንዳርዱ መሠረት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው ብለዋል።
በዘርፉ በፊት ያለውን ልምድ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ብቁ የሆኑ የውሃ አገልግሎቶችን ለመፍጠር ስልጠናው ወሳኝ ነውም ብለዋል።
ስልጠናውን የሚወስዱ አካላትም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ልምድ በመውሰድ ለሌሎች ማካፈል እንዳለባቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የውሃ ና ሳኒቴሽን ፌጀሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙክታር አህመድ የውሃ ኦፕሬተሮች አጋርነት በዋናነት በውሃና በሳኒቴሽን ዘርፋ ድጋፍ በማድረግ የተሻለ አገልግሎት እንዲኖር ለማስቻል ታላሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
ዩኒሴፍ በኢትዮጵያ በርካታ ድጋፎችን የማድረግ ረጅም እና የተሳካ ታሪክ አለው ያሉት አቶ ሙክታር አጋርነቱ አቅምን በመገንባት ፣ አዳዲስ አሰራሮችን በማስተዋወቅ ፣ ዘላቂ ማሻሻያዎችን በማድረግ የመፈጸም አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።
በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የከተሞች መጠጥ ውሃ ፣ሳኒቴሽንና ሀይጅን ስፔሻሊስት አቶ ባሳዝን ምንዳ ዩኒሴፍ በዘርፉ የተሻለ አቅም ባላቸው ሙያተኞች አቅምን የማሳደግና የሲስተም ማዘመን ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የአጋር አካላትን ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያም ከሶስት ከተሞች ወደ 18 ከተሞች በማስፋት የአቅም ግንባታ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ስልጠናው ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ከውሃና ሳኒቴሽን ፌደሬሽን ፣ከዩኒሴፍ ፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ከውሃ አገልግሎቾች የተውጣጡ የዘርፉ ሙያተኞች እየተሳተፉ ነው።