የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በዘላቂነት አገልሎት እንዲሰጡ በየደረጃው ያሉ የውሃ ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ተባለ።

የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በዘላቂነት አገልሎት እንዲሰጡ በየደረጃው ያሉ የውሃ ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ተባለ። ግንቦት 27/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ በየደረጃው ያሉ የውሃ ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ገለፁ። ውሃን ለማስተዳደር ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ተቋማት ናቸው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ከተገነቡ በኋላ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ እስከሚጠበቅባቸው የአገልሎት ዘመን እንዲደርሱ የተቋማት ክትትልና ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡ ክብር ሚንስትሩ እክለውም የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የተገነቡበትን ወጪ በመሸፈን የዜጎችን የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ የኢንቨስትመንት አማራጭን ለማስፋት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ ከተሞች የውሃና ሳኒቴሽን ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙክታር አህመድ 71 ከተሞችን በ11 ቁልፍ አፈፃፀም መለኪያ መሰረት በመመዘን ከሰው ንክኪ ነፃ በሆነ ቴክኖሎጂ በማወዳደር የመጠጥ ውሃ አገልግሎቶችን ደረጃ አስቀምጠናል ብለዋል፡፡ እውቅናው ጥሩ ለሰሩት ማነቃቂያ ሲሆን ሌሎችን ደግሞ የሚያበረታታ፣ በከተሞች መካከልም ጤናማ የውድድር መንፈስ እንዲፈጠር የሚያደርግ በመሆኑ ጥራት ያለው፣ በቂ፣ ዘላቂና ዘመናዊ የሆነ አገልግሎት አሰጣጥ በከተሞቻችን እንዲሰፍን እና የደንበኞች እርካታ እንዲረጋገጥ ያደርጋል ብለዋል። እያንዳንዱ ከተማ ምን እና እንዴት እንደሚሰራ የሚያሳየው ሲስተም ከዚህ በፊት ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም በተሻለ ደረጃ ለመጠቀም የሚኒ ቢዝነስ ፕላን፣ ታሪፍና ገቢ ያልተሰበሰበበት የውሃ ባላንስ በኦን ላይን እንዲያስገቡ የተሻሻለው የአሰራር ስርዓት በክቡር ሚኒስትሩ ይሁንታ አግኝቷልም ብለዋል። የአዳማ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር አህመድ አብዱልጀሊል በበኩላቸው ፎረሙ በክልል ከተሞች በውሃ አስተዳደር ላይ ጥሩ ተሞክሮዎችን በመቀመር ለለውጥ መዘጋጀት እና የእርስ በእርስ መማማር ብሎም አዳዲስ ስራዎችን ለማስተዋወቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል። አቶ አህመድ አክለውም የአዳማ መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ተጠቃሚን ከአቅርቦት ጋር በማጣጣም ፣ ከአደረጃጀት ጀምሮ የቡድን ስራን ተግባራዊ በማድረግ ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የውሃ አገልግሎት ተደራሽነት ቀልጣፍ እንዲሆን የተሰራው ስራ ውጤታማ በመሆኑ ዕውቅና እንደተበረከተላቸው ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ ሳኒቴሽንን ጨምሮ ከዚህ በላይ በመስራት ደረጃችንን እናስጠብቃለንም ብለዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የከተሞች የውሃ ፎረም ላይ መሳተፋቸውን የገለፁልን የሠመራ ሎጊያ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ጣሂሮ ሁሴን የከተሞች የመጠጥ ውሃ አገልግሎቶች በቁልፍ አፈፃፀም አመላካች (KPI) ተመዝነው ዕውቅና ካገኙት መካከል በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልፀው፤ እውቅናው በቀጣይ ዓመታት በተሻለ መልኩ ሰርተን የህዝቡን የውሃ አገልግሎት ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛ ሆነን እንድንሰራ ያነሳሳል ብለዋል። ከመድረክ ያገኘነውን ምርጥ ተሞክሮ በመቀመርና የውሃ ፍላጎትን ከአቅርቦት ጋር በማጣጣም ለምንሰራው ስራ ልምድ ያገኘንበት ፎረም ነውም ብለዋል።

Share this Post