የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሄራዊ ኢነርጂ ኮምፓክት ረቂቅ ሰነድ ላይ ተወያየ።
ግንቦት 27/2017ዓም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያካተተ የቴክኒክ ቡድን ባዘጋጀው የብሔራዊ ኢነርጂ ኮምፓክት ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ፡፡
መርሀ ግብሩን ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የስብሰባ ዋና አላማ በብሔራዊ ኢነርጂ ኮምፓክት ላይ በሁሉም ቁልፍ ባለድርሻ አካላት መካከል የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር በቀጣይ ሂደቱ ላይ በጋራ ርብርብ ለማድግ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በማከል ብሔራዊ ኢነርጂ ኮምፓክት ከዓለም ባንክ ቡድን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ አጋሮች ጋር በመተባበር ተልዕኮ 300 (Mission 300) የተሰኘና ከሰሃራ በታች ላሉ 300 ሚሊዮን ዜጎች የኤሌክትሪክ አቅርቦት እና ንፁህ የምግብ ማብሰያ መፍትሄዎችን ተደራሽ ለማድረግ የተነደፈውን ቀጠናዊ ኢኒሸቲቭ መሰርት አድርጎ መዘጋጀቱን አንስተው ሰነዱን ለማዳበር ሀሳብ አስተያየት እንዲሰጥበት አሳስበዋል ።
የብሄራዊ ኢነርጂ ኮምፓክት ረቂቅ ያቀረቡት አቶ ጎሳዬ መንግስቴ በአምስት ስትራቴጂካዊ የትኩረት መስኮችና ግቦች ያቀፈ ብሔራዊ ኢነርጂ ኮምፓክት መዘጋጀቱን በመጠቆም፤ በዋናነት ሁለንተናዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት እና የንጹህ የማብሰያ መፍትሄዎች፣ የንፁህ ኢነርጂ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት እና በታዳሽ የኢነርጂ ሽግግር፣ ቀጠናዊ ትስስር፣ የፋይናንስ ዘላቂነት እና የአሠራር ቅልጥፍና፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና ተቋማትን ማጠናከር መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በቀረበው ረቂቅ በተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች በዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ እና የገንዘብ ሚኒስትር ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ምላሽ ተሰጥቶበታል።
ከተልዕኮ 300 ጋር የተጣጣሙ የሃይል አቅርቦት እና ዘላቂ ግቦችን ለማሳካት ሀገራዊ ቁርጠኝነትን እንደሚጠይቅ ከውይይቱ ማወቅ ተችሏል ።