የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ልኡካን እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያዩ፡፡
ግንቦት 22/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ልኡካን እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉ አመራሮች በተገኙበት በፕሮጀክቶች አፈጻጸምና ቀጣይ ሊደረጉ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡
በአፍሪካ ልማት ባንክ የሚደገፉ የ4 ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እና የቦረና የውሃ ልማት ለተሻሻለ ኑሮ ፕሮግራምን በተመለከተ በአፍሪካ ልማት ባንክ ልኡካን ለ10 ቀን ሲከናወን የቆየውን ዓመታዊ የባንኩን ተልዕኮ አስመልቶ የመዝጊያ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ከ4ቱ ከተሞች የጎዴ እና ቢቸና ከተሞች የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸዉ ፣ የአዳማ ከተማ መጠጥ ውሃ አፈጻጸም 95 ፐርሰንት መከናወኑና በከፊል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ፣ የመቀሌ ከተማ 42.6 በመቶ የደረሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የቦረና የውሃ ልማት ለተሻሻለ ኑሮ ፕሮግራም የምዕራፍ አንድ አፈጻጸም 37.5 በመቶ ሲሆን በምዕራፍ 2 ደግሞ ከፊል ስራዎች መጀመራው ተመላከቷል፡፡
በባንኩ ልኡካን በኩልም ለ4ቱ ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ከ76 ሚሊየን ዶላር በላይ ብድር ማበደራቸውን እና ለቦረና ፕሮጀክት ደግሞ 70 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ መስጠታቸውን ገልጸው አፈጻጸሙም በመልካም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋዉ ዲንጋሞ ያልተጠናቀቁ ፐሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የተያዘላቸውን ግብ እንዲመቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝና የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸምም በአጥጋቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ባንኩ ተጨማሪ ድጋፍ እና ብድር እንዲያደርግም ክቡር አምባሳደሩ ጠይቀዋል፡፡