ክቡር ሚኒስትሩ ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ፡፡
ግንቦት 21/09/2016 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚ/ር ሉዊስ አንቶይን ሶሸ ጋር ተወያዩ፡፡
በውሃ ልማት ፈንድ በኩል እየተተገበረ በሚገኘው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም ላይ ትኩረት አድርጎ በተካሄደው ውይይት ሚ/ር ሉዊስ አንቶይን ሶሸ ፕሮግራሙን የበለጠ ውጤታማ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና ቀጣይ በሚደረጉ ድጋፎች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የከተሞች የውሃ አገልግሎት ተቋማትንም አቅም ለመገንባት ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ጋር እንደሚሰሩም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው የውሃ ልማት ፈንድ ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ አስፈላጊው እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ የአደረጃጀት፣ የፕሮግራም አመራር እና አተገባበር ሂደቶች ላይ የላቀ አፈጻጸም ሊያመጣ በሚችል መልኩ እንደሚታይ አንስተዋል፡፡ ለዚህም የአስተባባሪ ኮሚቴ እንደሚደራጅ ገልጸዋል፡፡
የከርሰምድር ውሃ ፍለጋ ጥናት ከምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባሻገር በሌሎች መሰል ፕሮግራሞች ባልታቀፉ ሌሎች ክልሎች መተግበር እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትሩ አንስተዋል፡፡
በውይይቱ የፈረንሳይ መንግስት በኢነርጂ ልማት ዘርፍ፤ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና እና በከርሰምድር ውሃ ጥናት ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡