የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በማሳካት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አስቻይ የውሃ እና የኢነርጂ ፖሊሲዎች ማዘጋጀት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ግንቦት 18/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃና ኢነርጂ ረቂቅ የፓሊሲ ሰነዶች ላይ በመከረበት መድረክ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን በማሳካት የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አስቻይ የውሃ እና የኢነርጂ ፖሊሲዎች ማዘጋጀት ወሳኝ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
ፖሊሲዎቹ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር ውጤታማ ስራ ለመስራት ወሳኝ መሆናቸው ተገልጿል።
የውሃ ሀብት አስተዳዳር ዘርፍ አማካሪ አቶ በላይነህ ይርዳው በውሃ ላይ የተዘጋጀውን ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ አስፈላጊነት፣ መርሆዎችና ዓላማዎቹን በዝርዝር አቅርበዋል።
ፖሊሲውን ማሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያት እና ከትግበራ በኋላ ስለሚገኘው ውጤትም አብራርተዋል።
አስተማማኝ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፣ የተሻሻለ የሳኒቴሽን አገልገሎት ፣ ዘላቂነት ያለው የውሃ ሀብት ግኝትና ምደባ ፣ የተረጋገጠ የተፋሰስና የውሃ አካላት ደህንነት ፣ የሀገሪቱ የውሃ ሀብት ብሄራዊ ደህንነት ጥቅም ማረጋገጥ ምን ሊሆን እንደሚችል እና ተያያዠ ጉዳዮች ፖሊሲው ያተኮረባቸው መሆኑንም በስፋት አብራርተዋል።
የኢነርጂ ልማት ዘርፍ አማካሪ የሆኑት አቶ ጎሳዬ መንግስቴ የኢነርጂ ረቂቅ ፓሊሲ የትኩረት አቅጣጫዎችን በስፉት አብራርተዋል።
የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽነት ማረጋገጥ፣ ንፁህና ታዳሽ የማብሰያ ቴክኖሎጂና ኢነርጂ ተደራሽነት ማረጋገጥ፣የታዳሽ ኢነርጂ ቅልቅል እና ተጓዳኝ መሰረተ ልማቶች ማስፋፋት፣ የኤሌክትሪክ ዘርፉን የፋይናንስ ጤናማነት እና የአገልግሎት ጥራት አስተማማኝ ማድረግ፣ ለቀጠናው የሚቀርበውን የኃይል ሽያጭ በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን አስተማማኝ ማድረግ፣ የኢነርጂ አጠቃቀም ብቃት እና ቁጠባን ማሳደግ ፖሊሲው ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም በስፋት አብራርተዋል።
በቀረቡት ሁለት ረቂቅ የፖሊሲ ሰነዶች ዙሪያ ከተሳታፊዎቹ ሰፊ ሀሳብ እና አስተያየቶች ተንጸባርቀዋል።
ፖሊሲዎቹ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማጠናከር ትልቅ አቅም እንዳላቸውና ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚያስችሉም ተገልጿል።
ረቂቅ ፓሊሲዎቹን ሊያዳብሩ የሚችሉ እና በአተገባበራቸው ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ ሰፋፊ ሀሳቦች ተነስተዋል።
በተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ላይም ውይይቱን በመሩት የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ እና በሚኒስትር ዴኤታ ማእረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ በክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በውይይት መድረኩ የውሃ ፣ መስኖ ፣ ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፣ የክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላትና አጋር የልማት ድርጅቶች ተሳትፈዋል።