ትውልዱ የውሃ ተመራማሪ፣ ተደራዳሪና ዲፕሎማት እንዲሆን በትምህርት ተቋማት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ።
ግንቦት /2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ባዘጋጁት 12ኛው የውሃና የውሃ ዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ ላይ ትውልዱ የውሃ ተመራማሪ፣ ተደራዳሪና ዲፕሎማት እንዲሆን በትምህርት ተቋማት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ መድረክ ላይ ትውልዱ ስለ ሀገሩ የውሃ ሀብት በሚገባ ተገንዝቦ ተመራማሪ፣ ተደራዳሪና ዲፕሎማት እንዲሆን በትምህርት ተቋማት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
በውሃ ሀብት ዙሪያ ለትብብር ቁርጠኛ መሆናችንን በማሳየት ቀጣይነት ያለው ፣ በመረጃ የተደገፈና ውጤታማ የሆነ የውሃ ልማት ዲፕሎማሲ እየተገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም አለምአቀፍ ተሞክሮን ለመቀመርና የውሃ ዲፕሎማሲያችንን ለማጠናከር በውሃው ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን፣ የምርምርና የሚዲያ ተቋማት በጋራ መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የህዝብ ተ/ም/ቤት አባልና የህዳሴው ግድብ ተሟጋች የተከበሩ አቶ መሀመድ አልአሩሲ በበኩላቸው ውሃ የሀገራችን የዲፕሎማሲ ትኩረት ከመሆንና እና አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ የባህር በር ጥያቄያችንንም ሊመልስ የሚገባ አጀንዳ መሆን አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ ያላት ሀገር በመሆኗ ከውሃ ጋር በተያያዘ በቀጣዩ ትውልድ ታሪክ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት የገለጹት የተከበሩ አቶ መሀመድ አልአሩሲ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ሆነ በውሃው ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።
ከዚህ በፊት በተካሄደው ኮንፈረንስ በአባይ ቤዚን ላይ ብቻ ያተኮረ ፅሁፍ ይቀርብ የነበረ ቢሆንም በ12ኛው የውሃና የውሃ ዲፕሎማሲና ኮንፈረንስ ላይ ደግሞ የኦሞ ጊቤ ቤዚን የተዳሰሰበትና አዳዲስ ምሁራን የተቀላቀሉበት በመሆኑ የበለጠ ግብዓት ተገኝቶበታል ተብለዋል።
በኮንፈረንሱ የዘርፉ ምሁራን ባቀረቧቸው ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በመድረኩ ኢ/ር ጌዲዮን አስፋው፣ አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ፣ ኢ/ር ተፈራ በየነ እና አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ የተሳተፉበት የፓነል ውይይት ተካሂዷል።