ተግባር ተኮር ስልጠናው ደህንነቱ የተጠበቀና ጥራት ያለው የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ተባለ።
ሚያዝያ 07/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዳማ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ተግባር ተኮር ስልጠናው ደህንነቱ የተጠበቀና ጥራት ያለው የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ተብሏል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታምሩ ገደፋ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ እና የመጠጥ ውሃ ጥራት ስታንዳርድ ማዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የውሃ የቢዝነስ ዕቅድ (Business plan) ሳይኖር የውሃ ታሪፍ መጨመርና መቀነስ አይቻልም የሚሉት አቶ ታምሩ መሬት ሊወርድ የሚችል፣ በማንና እንዴት ሊተገበር የሚገባና የውሃ ገቢን የሚያሳይ ዕቅድ ያስፈልጋልም ብለዋል።
በአፋር ክልል በም/ር/መስተዳደር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ አሊ መሀመድ መርሃ ግብሩ የአመራሩን ቁርጠኝነትና ራዕይ ያላቸው መሆኑን ያየንበት ነው ብለዋል።
ተሳታፊዎቹ ይሄንን ተሞክሮ ወደ ህብረተሰቡ በማውረድ በአገልግሎታችን ሲረኩ ነው እድገታችንም የሚረጋገጠው ብለዋል።
አክለውም እንደ አፋር ክልል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚያደርግልን ድጋፍ፣ ስልጠናውን ለሰጡንና ልምድ ያካፈሉን የአዳማ ከተማ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲሁም ይሄንንም መድረክ ያመቻቹልንን ሁሉ እናመሰግናለን ብለዋል።
የአዳማ ከተማ መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ም/ስራ አስኪያጅና የቴክኒክ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካሳ በኩረ የአዳማ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ብዙ ተግዳሮቶችን አልፈው ለዛሬው ስኬት የበቁት በቅንጅታዊና በአመራር ቁርጠኝነት መሆኑን አስረድተው ከስልጠናውንም ሆነ ከመስክ ምልከታው ያገኙትን እውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል የአዳማ መጠጥ ውሃ አገልግሎት የውሃ ጥራትና ምርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢ/ር ወርቁ ተሾመ በመስክ ምልከታው ወቅት የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ጥራትን እንዴት እንደሚቆጣጠሩ፣ እንደሚከታተሉና እንደሚያስተዳድሩ ገለፃ አድርገው፤ ሰልጣኞቹ በስራቸው ላይ ለሚገጥማቸውና ለሚጠይቁት ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ፍቃደኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት በየከተማው ባለው የውሃ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያገኙትን ልምድ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።