የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አማካሪ ድርጅት የቅድመ ጥናት ሪፖርት ለውይይት ቀረበ፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አማካሪ ድርጅት የቅድመ ጥናት ሪፖርት ለውይይት ቀረበ፡፡ ግንቦት 07/2017ዓም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አማካሪ ድርጅት የቅድመ ጥናት የከርሰ ምድር ውሃ አቅም ግምገማ፣ ዝርዝር የዳሰሳ ሃይድሮጂኦሎጂ ጥናት፣ የከርሰ ምድር ውሃ አዋጭነት ጥናት፣ የኮንትራት አስተዳደር ሪፖርት ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ኮርድኔተር ዶ/ር ከበደ ገርባ ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ሶስት አመት ማስቆጠሩን ገልጸው በከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ልየታ፣ የመጠጥ ውሃ ግንባታ እና መስኖ ላይ ከፍተኛ በጀት ተበጅቶለት እየተተገበረ ያለ ፕሮጀክት ነው ብለዋል፡፡ ከ1.5 ሚሊየን በላይ የህረተሰብ ክፍሎችን በመጠጥ ውሃ መተጠቃሚ ለማድረግ በ67 ወረዳዎች የከርሰ ምድር ውሃን በብዛት እና በጥራት እንዲሁም ወደፊት እንዴት ማስተዳደር እንደሚገባ ለመለየት የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ እየተተገበረ ነውም ብለዋል፡፡ እየቀረበ ያለው ጥናት የሀገራችንን 10 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን 1ለ50 የሚባል የሀይድሮሎጂ ካርታ በማዘጋት የሀገራችንን የከርሰ ምድር ውሃ ዝርዝር የምናውቅበት ሲሆን ይህም ከአሁን በፊት የነበረውን ዳታ ወደ 28 ከፍ የሚያርግ ነው ብለዋል፡፡ የከርሰምድር ውሃ ልየታውንና ጥናቱን ለመስራት 15 ድርጂቶች ተቀጥረው እየሰሩ መሆናቸውንም ዶ/ር ከበደ ገልጸዋል፡፡ በአለም ላይ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ በገጸ ምድር ውሃ ላይ ያለው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ የከርሰ ምድር ውሃ ደግሞ ይህንን ለመቋቋም የተሻለ አቅም ስላለው ጥናቱ ሀገራችን የአየር ንብረት ለውጡን እንዴት መቋቋም እንደምትችል መረጃ ስለሚሰጥ ያለንን የውሃ ሀብት ለማልማት ፣ ለመጠበቅ እና ለመንከባበክ እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡ በፕሮገራሙ ላይ በሶማሌ፣ ጀረር ፣ ሞጣ ፣አሶሳ በቆጂ የሚታዩና አማካሪዎች የደረሱበትን የጥናት ግኝቶች እንደሚቀርቡ ማወቅ ተችሏል፡፡

Share this Post