ውሃን በአግባቡ በማስተዳደር ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ።
ግንቦት 06/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት አቅርቦትን ዘላቂ ለማድረግ የውሃ ደህንነት ዕቅድ ትግበራ ዙሪያ በተዘጋጀ መድረክ ውሃን በአግባቡ በማስተዳደር ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች መካከል የውሃ ጥያቄ አንዱ መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትሩ በውሃ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲተገብሩት አሳስበዋል።
የውሃ ፕሮጀክት ስኬታማነት የሚለካው ፕሮጀክት በመገንባት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡን ዘላቂና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲቻል ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን የውሃ አያያዝ ግንዛቤ በማሳደግ በታሪፍ ላይ የተመሠረተ ወቅታዊ የውሃ አገልግሎት ክፍያ መሰብሰብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአፋር ክልል በም/ር/መስተዳደር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ክቡር አቶ አሊ መሀመድ በበኩላቸው መድረኩ ትልቅ ግብዓት ያገኘንበትና አቅም የሚፈጥርልን በመሆኑ በክልላችን ላይ ምን አቅም አለን፤ የት መድረስ አለብን፣ ሙያተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ሙያዊ ስነምግባር ተላብሰን ብልፅግናን ማረጋገጥ እንዳለብን የተማርንበት በመሆኑ ክቡር ሚኒስትሩም ለሰጡን አስተያየትና የስራ አቅጣጫ እናመሰግናለን ተብለዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ከመድረክ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።