በኢነርጅ ዘርፍ የፖሊሲ ክለሳ መደረጉ የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር የሚያስችል መሆኑ ተገለፀ።
ግንቦት 6/2017፡- (ው.ኢ.ሚ) ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025 ቢዝነስ ፎረም ላይ የኢነርጂ ፖሊሲ ክለሳ መደረጉ ኃይልን በማመንጨት ማሰራጨት እና ማስተላለፍ ላይ የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመሩ ተገለፀ።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በማንኛውም አይነት የኢኮኖሚ ልማት አስተማማኝ ፣አዋጭ እና ቀጣይነት ያለው የኢነርጂ አቅርቦት ቅድሚያና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በስፋት እያደገ የመጣው የሀገር ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለማስቀጠል ብሎም የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ አስተማማኝ ኢነርጂን ማቅረብ ምትክ የሌለው አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም የኢነርጂ ፖሊሲ ክለሳ መደረጉ ለግሉ ዘርፍ ኃይልን በማመንጨት የማሰራጨት እና የማስተላለፍ ተግባር ላይ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል፡፡
አክለውም በጋራ መበልጸግ በሚል መርህ የሀይል አቅርቦት ለጎረቤት ሀገር እያቀረብን መሆኑ እና መሰል ተግባራት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን እንደፈጠርን ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመን ፖሊሲ በመሻሻሉ በሀገር ውስጥ የተጀመሩ መልካም ተሞክሮዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የኢንዱስትሪ ፣ የማዕድን ፣የገብርና ፣የአይ ሲቲ እና የቱሪዝም ዘርፎች ከፍተኛ ኢነርጂ ከመፈለጋቸው አንጻር በቀጣይ ለጀመርናቸው ስራዎች መሳካት እንዲቻል ሀይል የማመንጨት ስራችን ማሳደግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ከዚህ በፊት 90 በመቶ ሀይል የምናመነጨው ከሀይድሮ ፓወር ብቻ ቢሆንም አሁን ላይ ያሉንን የተፈጥሮ ጸጋዎች በመጠቀም የሀይል አማራጮችን ማስፋት ግድ ይላል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ያለው የመንግስት አቅም ውስን በመሆኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን ከግብ ለማድረስ አስተማማኝ ሀይል ለማመንጨት የግሉ ዘርፍ ተቀዳሚ ሚናና ተሳትፎ አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡