የውሃ አገልግሎት ደህንነትን በማስጠበቅ ዘላቂ የውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
አዳማ:-ሚያዝያ 05/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ አገልግሎት ደህንነትን በማስጠበቅ ዘላቂ የውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሀይማኖት በለጠ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሁሉም ክልሎች በከተሞችና በገጠር መጠጥ ውሃ ተቋማት ላይ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና በአፋር ክልል የከተሞች መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመንና የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ ብሎም የውሃ አገልግሎት ተቋማትን አቅም ማጎልበት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አቶ ሀይማኖት አክለውም የመድረኩ አላማ የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አሰጣጥ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰና ማህበረሰቡን እንዴት ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ በመስክ ምልከታ የተደገፈ ልምድ በመውሰድ አቅምን ለማጎልበት ታላሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የሰመራ ከተማ የአምስት አመታት የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ቁልፍ የአፈጻጸም መለኪያ (KPI) ትንተናን ጨምሮ ሌሎች ፅሁፎች ቀርበው በሰፊው ውይይት የተደረገ ሲሆን የአፋር ክልል የውሃ ፌዴሬሽን እንደሚቋቋምም ተገልጿል።
በመድረኩም የአፋር ክልል በም/ር/መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ የኦሮሚያ እና አፋር ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ፣ የአዳማ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ እና የኢትዮጵያ ከተሞች የውሃ ፌዴሬሽን ሀላፊዎች እየተሳተፉ ነው፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ጋር በጋራ መድረኩን አዘጋጅተውታል፡፡