ፍትሀዊ ፣ ቀልጣፋና ዘላቂነት ያለው የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ጠንካራ አስተዳደር ፣ የሰለጠነ ባለሙያና የአሰራር ስርዓቶችን መገንባት እንደሚገባ ተገለጸ።
ግንቦት /2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ ) ፍትሀዊ ፣ ቀልጣፋና ዘላቂነት ያለው የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ጠንካራ አስተዳደር ፣ የሰለጠነ ባለሙያና የአሰራር ስርዓቶችን መገንባት ያስፈልጋል ተብሏል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከFCDO, ከዩኒሴፍና ከአዳማ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ኢንተርፕራይዝ ጋር የውሃ አገልግሎቶችን አቅም ለማጎልበት በአዳማ በተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት መድረክ ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ንግግር አድርገዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ውሃ እና ሳኒቴሽን የህይወት ፣ የጤናና የዘላቂ ልማት መሠረት በመሆናቸው በዘላቂነትና በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ ጠንካራ አስተዳደር ፣ የሰለጠነ ባለሙያና የአሰራር ስርዓቶችን በተገቢው መንገድ መገንባት ግድ ይላል ብለዋል።
ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከFCDO, ከዩኒሴፍ፣ ከውሃ አገልግሎቶች ፌደሬሽንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የ18 የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተቋማትን አቅም በማጎልበት አፈጻጸምን ለማሻሻል ያለሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።
በእስካሁኑ የትግበራ ሂደት በተደረጉ የውይይት መድረኮች የተገኘ እውቀትና ልምድም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ሊለካ የሚችል መሻሻሎችን አሰገኝቷል ብለዋል።
ተጠያቂነት፣ ግልጸኝነትና ለውጥ የሚያመጣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስተማማኝና ፍትሃዊ የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ለመስጠት ቁልፍ መሆኑንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል።
መድረኩ ሙያተኞቹ በአተገባበር ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ላይ በመወያየት ምርጥ ተሞክሮዎችን የሚጋሩበትና አዳዲስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጡበት ነውም ብለዋል።
ሀሉንም ኢትዮጵያዊ ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የመንግስት ፣ የልማት አጋሮች፣ የውሃ አገልግሎቶችና የማህበረሰቡ ቅንጅታዊ አሰራር የበለጠ መጠናከር እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ለዘርፉ ስኬት ወሳኝ የሆነውን የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ እንዲሁም ንቁ ተሳትፎና አጋርነትን ያሳዩትን ክቡር አምባሳደሩ አመስግነዋል።
በመድረኩ ከውሃና ኢነርጂ ፣ከልማት አጋሮች ፣ከውሃ አገልግሎቶች ፌደሬሽን ፣ ከአዳማ ከተማ ውሃና ፍሳሽ ኢንተርፕራይዝና ከግሉ ዘርፍ የተወከሉ እየተሳተፉ ነው።