በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግቢ የተገነባው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውና ትልቁ ከባዮጋዝ ኤሌኬትሪክ የሚያመነጨው ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
ሚያዚያ 22/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከቻይና መንግስት ፣ ከዩኤን ዲፒ እና ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያውና ትልቁ ከባዮጋዝ ኤሌኬትሪክ የሚያመነጨው የባዮጋዝ ፕሮጀክት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግቢ አስገንብቶ አስመርቋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የፕሮጀክቱን ስራ መጀመር በስፍራው ተገኝቸው አብስረዋል።
ፕሮጀክቱ 300 ሜትር ኪዩብ የማብለያ አቅም አለው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የባዮጋዝ ምርትን ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር 20ኪሎ ዋት ሀወር ሀይል በማምረት የዩኒቨርሲቲውን የማብሰል ሂደት መሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ በመተካት ጤናማ ያደርጋል ብለዋል ።
አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቀመው ባዮ ማስ የካርበን ኢሚሽንን በመጨመር ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ በማስከተል ለተለያዩ የጤና እክሎች ይዳርጋል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ለመከላከል የባዮ ጋዝ ፕሮጀክቶች ከቤተሰብ ባለፈ በተቋማት ደረጃ በስፋት ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ብለዋል።
እንደ ሀገር በዓመት ለአፈር ማዳበሪያ የሚወጣውን 1.3 ቢሊየን ዶላር በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመተካት ፕሮጀክቱ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ወ/ማርያም የባዮ ጋዝ ፕሮጀክቱ ለመብራት እና ለማብሰል አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የሚገኘው ማዳበሪያ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዘውድነህ ቶማስ በምስራቅ አፍሪካ የመደመሪያ የሆነው የባዮጋዝ ፕሮጀክቱ የቻይና ፣የዩኤን ዲፒ እና የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች ምርምር የሚያደርጉበት ማእከል በመሆን የሚያገለግል ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ዶክተሩ ለዚህ ፕሮጀክት ውጤታማነት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ቅንነት እንዲሁም በፕሮጀክቱ የተሳተፉትን በሙሉ በእጅጉ አመስግነዋል።
ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በአመት 87,600 ኪሎ ዋት ሀወር ሀይልን በመቆጠብ በአመት የሚወጣውን 12,950,000 ብር ወጭ ይቆጥባል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ የጭስ ልቀትን በመቀነስ በጭስ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ከመከላከል ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ የሚያበረክተው አስተዋጽ የጎላ ነውም ተብሏል።
በቀን 4.7 ቶን ተረፈ ምርት ለፕሮጀክቱ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን አንዴ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ማንኛውንም ኦርጋኒክ የሆነ ተረፈ ምርት ስለሚጠቀም ዩኒቨርሲቲ ላይ መገንባቱ ጥሩ አጋጣሚ ነውም ተብሏል።
በመርሃ ግብሩ ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ፣ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ም/ ፕሬዘዳንት ተገኝተዋል።