የተፋሰስ ሀብት መረጃ ክትትል ስትራቴጂ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን እውን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ ተገለፀ።

የተፋሰስ ሀብት መረጃ ክትትል ስትራቴጂ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን እውን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ ተገለፀ። ሚያዝያ/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በብሉ ዲል ባለሙያዎች የተዘጋጀው የተፋሰስ ሀብት መረጃ ክትትል ስርዓት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን እውን ለማድረግ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ ተገለፀ። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የተፋሰስ ክትትል ስትራቴጂ ሰነድ ያዘጋጁትን አመስግነው ከውይይቱ የተገኙ ግብአቶችን በማካተትና ሰነዱን በማዳበር ለቀሪ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የቀድሞው የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ በሰጡት አስተያየት ሰነዱ የተቋሙ የመረጃ ምንጭ በመሆኑ እንደሀገር የሚጠበቀውን ልማት ለማፋጠን የገፀ ምድር፣ የከርሰ ምድርና የውሃ ጥራት ሁኔታ ተለይቶ መታወቅ አለበት ብለዋል። የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ የክትትል ሳይቶች ዲዛይን መደረግ አለበት ያሉት ዶ/ር አብርሃ አርብቶና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፓይለት ፕሮጀክቶች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል። የተዘጋጀው የተፉሰስ ሞኒተሪንግ ስትራቴጂ በቀጣይ ለሚመለከታቸው ባለድርሻዎች የሚቀርብ ሲሆን ከፀደቀ በኋላ በተቋሙ ያሉ የ One- WaSH ፕሮጀክቶች በበጀት እንደሚደግፍ ተጠቁሟል። የተዘጋጀው የተፋሰስ ሀብት መረጃ ክትትል ስርዓት (Basin Monitoring Strategy) ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ የበላይ አመራሮች ለውይይት ቀርቦ ይሁንታን ከማግኘት ባሻገር ጥሩ ግብአት የተገኘበት መሆኑን የገለፁት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ከዚህ በፊት የተዘጋጀው ቤዚን ፕላን በምን አግባብ መመራትና የት ቦታ ምን አይነት መረጃ አለ የሚለውን ለማስተዳደር ያስችላል ብለዋል። የአሰራር ስርዓቱን ማዕከላዊ በማድረግ የሰው ሀብቱንና የፋይናንሱን የስታንዳርድ ጥያቄ ይመልሳልም ብለዋል። ሰነዱ ጥናቶችን በማሰባሰብ፣ ከአሁናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማጣጣም፣ ከማህበራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ የተሻለ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲኖር ብሎም ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ በሚያስችል መንገድ የተዘጋጀ ነው ብለዋል አቶ ደበበ። የመረጃ ስርዓት ላይ ትልቅ ለውጥ በመኖሩ Citizen Scientists የሚያመጡትን የ Remote Sensing መረጃ ታሳቢ በማድረግ የውሃ መረጃ ላይ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን በሚወጣበት አግባብ የተዘጋጀ በመሆኑ ለ10 አመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ሆኖ እንደሚያገለግልም ተገልጿል።

Share this Post