የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች በመሀሉ ዘመን ሰነድ ዙሪያ ተወያዩ።
ሚያዚያ 22/2017 ዓ/ም ውኢሚ
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች በመሀሉ ዘመን ሰነድ ዙሪያ ተወያይተዋል።
የውይይቱን መድረክ የስጀመሩት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትር የመሀሉ ዘመን ሰነድ ይዘት ከተቋም ተግባራት አለፍ ባለ ሁኔታ አስተሳሰባችንና አመለካከታችንን እንደ ሀገርና እንደ አለም አቀፍ እንድንቃኝ የሚያደርገን በመሆኑ ተሳታፊዎች ሰነዱን ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል
የመሀሉ ዘመን ሰነድ ያቀረቡት ክቡር ዶ/ር ዘለቀ ተመስገን የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር የመሀል ዘመን የሚባለው እንደ ሀገር የትጋትና የስኬት ገጽታ ሲሆን ወደ መዳረሻችን ገጽታ ከመድረሳችን በፊት ያለው የመሀሉ ዘመን እንደሚባል አብራርተዋል።
የኖኪያን ካምፓኒ የናይጄሪያንና የቬትናምን የ1970ቹን ከፍተኛ ስኬት የወለደውን መዘናጋትና ውድቀት በመረጃ አስደግፈው በማብራራት እንደ ሀገር ከነዚህ ሀገራትና ካምፓኒ ትምህርት በመውሰድ መጠንቀቅ ይኖርብናል ብለዋል።
ክቡር ኮሚሽነሩ የለውጡን ዋዜማ ፣የለውጡን መባቻና በለውጡ ወቅት የነበሩ ተግዳሮቶችንና ስኬቶችን አውስተው ተግዳሮቶቹን እንዴት በድል ማለፍ እንደተቻለም አብራርተው በዓለም ሀገራት የሀይል አሰላለፍ ውስጥ የኢትዮጵያ አቅም እንዴት እንዳደገና ምን ውጤት እንደመጣም ገልፀዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ከመድረኩ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ እንደሀገር ካለፉት ተግዳሮቶች በመማር ሁላችንም ለሀገር ሰላምና ዕድገት ተግተን መስራት አለብን ተብሏል።