የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን ውብ ፣ ፅዱና ምቹ ከተማ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።

የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን ውብ ፣ ፅዱና ምቹ ከተማ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ። ሚያዚያ/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ከክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮና ከከተማው የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ ኮርፖሬሽን ጋር በመቀናጀት 14 የጋራና 26 የህዝብ ዘመናዊ መፀዳጃ ቤቶችንና የገላ መታጠቢያዎችን አስገንብቶ አገልግሎት ላይ መዋሉን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ቡድን በቦታው በመገኘት ዘግቧል። አቶ ሀብታሙ ፈንታ የወላይታ ሶዶ ከተማ የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን የወላይታ ሶዶ ከተማን ውብ ፅዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ከተማ ለማድረግ ዘመናዊ የህዝብና የጋራ መጸዳጃ ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልፀዋል። የመጸዳጃ ቤቶቹ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደተገነቡ የገለጹት አቶ ሀብታሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በከፍተኛ ቅንጅት በመስራታቸው ስራውን የተሳካ እንዲሆን አግዟል ብለዋል። የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተባባሪ አቶ ሙሴ ገ/ስላሴ እንዳሉት 26 የህዝብ እና 14 የጋራ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃና ገላ መታጠቢያ ቤቶች እንደተገነቡ ገልፀው በተደራጁ ማህበራት አማካኝነት የገቢ መሰብሰብና የቁጥጥሩ ስራው በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ ዘመናዊና ቀጣይነት ያለው እንዲሆንም በ10 ሄክታር መሬት ላይ ዘመናዊ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ እየተገነባ መሆኑንና እሰከ ሐምሌ 2017 ዓ.ም ሊጠናቀቅ እንደሚችልም አቶ ሙሴ አክለው ገልፀዋል። የከተማዋ ነዋሪ፣ አካል ጉዳተኛና የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑት አቶ ማሞ ሾርሞ አዲሶቹ መፀዳጃ ቤቶች ከመገንባታቸው በፊት ሁሉም የአካባቢው ነዋሪ በአንድ በፈራረሰና ሞልቶ በሚፈስ መፀዳጃ ይጠቀሙ እንደነበርና በተለይም እንደሳቸው አካል ጉዳተኛ ለሆነ ሰው እጅግ ፈታኝ እንደነበረ ገልፀው አሁን ግን ምቹና ጽዱ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል። የገነባላቸውን የመንግስት ተወካዮች በሙሉም አመስግነዋል፡፡

Share this Post