ስለውሃ ጥራት የሚቆጭ፣ የሚቆረቆር፣ ዕሴት የሚጨምርና ሰፊ ዕይታ ያለው ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
ሚያዝያ 03/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በማህበረሰብ አቀፍ የውሃ ጥራት ክትትል ስራ (Citizen Science) ፕሮጀክት ዙሪያ በሚሰጠው የተግባር ተኮር ስልጠና ላይ ስለውሃ የሚቆጭ፣ የሚቆረቆር፣ ዕሴት የሚጨምርና ሰፊ ዕይታ ያለው ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ስልጠናውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የሀዋሳ ሀይቅ ብዙ ጫና ያለበት በመሆኑ የውሃ ጥራት ቁጥጥር ስራውን ለማገዝ የአካባቢው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በመጠቀም ብቸኛ አማራጭ ነው ብለዋል።
አቶ ደበበ አክለውም የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ በሚሰራው ስራ ወጣቱን ስለውሃ ሀብት ደህንነት ግንዛቤ በማስጨበጥ የውሃ አካላት ደህንነት የሁሉም ዜጋ ጉዳይ በመሆኑ በሀይቁ ዙሪያ ያሉ ፍቃደኛ ወጣቶችን መጠቀም ይገባልም ብለዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ የውሃ ጥራት ክትትል ስራ (Citizen Science) ጥራት ያለውና በቴክኖሎጂ የታገዘ መረጃ መሰብሰብ ያስችላል ያሉት አቶ ደበበ የውሃ ጥራት ክትትል ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ መረጃዎች ተሰብስበውና ተደራጅተው ወደዳታ ቤዝ ስለሚገባ ከስልጠናው በኋላ ሁሉም Citizen Scientists የክትትል ስራውን በአግባቡ እንዲሰሩ፤ ለሚያስፈልጋቸውም ቴክኒካል ድጋፍ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
የኢኮሀይድሮሎጂና የውሃ ጥራት ዴስክ ተ/ኃላፊ አቶ ይርጋለም እሱነህ በበኩላቸው በሀዋሳ ሀይቅ አካባቢ የሚኖሩ Citizen Scientists በተለየ መልኩ ህይወታቸው ከሀይቁ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ከሌላው ማህበረሰብ ይልቅ የውሃውን መበከል የሚያውቁበት መንገድ በመኖሩ፤ በሀይቁ ዙሪያ የሚሰሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን መርጦ በማሰልጠን በየወሩ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የውሃውን ጥራት እየተከታተሉ ትክክለኛ መረጃን በመስጠትና የGIS መተግበሪያን በመጠቀም ወደ መረጃ ቋት በማስገባት ውሳኔ ሰጪ አካላትን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለዋል።
አቶ ይርጋለም አያይዘውም ወጣቶቹ የሀገር በቀል ዕውቀታቸውን ተጠቅመው የውሃ ብክለት ደረጃን በመለየት፤ ከማህበረሰቡና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመወያየትና የመፍትሄ ሃሳብ በማመንጨት የውሃ ሃብታችንን ዘለቄታዊ ጥቅም በማረጋገጥ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ያግዛሉ ብለዋል::
በውሃ ጥራት መመርመርመሪያ እና መተግበሪያውን በመጠቀም እንዴት የውሃ ጥራት ክትትል እንደሚደረግ ከ Earthwatch ተቋም የአለም ዓቀፍ Citizen Science ፕሮጀክት አስተባባሪ በDr. Steven Loiselle ለሚኒስቴር መ/ቤቱ የኢኮሀይድሮሎጂና የውሃ ጥራት ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
ከ23 ዓመት በላይ በሀይቅ ላይ የሰሩት አቶ መላኩ ጋንብር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሀይቁን የውሃ ደህንነት አስጠብቀን በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጥ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስልጠና ወስደን የውሃ ጥራት ክትትል እንድናደርግ እድል በማግኘታችን ሚኒስቴር መ/ቤቱን እናመሰግናለን ብለዋል።
በሀዋሳ የፍቅር ሀይቅ ማህበር ግዥና የጀልባ ኦፕሬተር አቶ አንሙት ፈይሳ ስልጠናው በቴክኖሎጂ የታገዘ የውሃ ጥራት ክትትል ስራን ለመስራት የተሰጠን ስልጠና ከጠበቅነው በላይ ብዙ ነገሮች እንድናውቅ አግዞናል ስልጠናውን ያስተባበሩትም ሆነ ስልጠናውን የሰጡን ባለሙያዎች በማህበሩ ስም አመሰግናለሁ ብለዋል።
በ10 የክትትል ጣቢያ ላይ ለሚሰሩ 20 ማህበረሰብ አቀፍ የውሃ ጥራት ክትትል በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች (Citizen Scientists) ለሁለት ተከታታይ ቀናት ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በሀዋሳ ፍቅር ሀይቅ ዙሪያ የሳይት ርክክብ ተደርጓል።