የቶጎጫሌ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ፡፡

የቶጎጫሌ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ፡፡ ሚያዝያ 04/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) ከ56 ሽህ በላይ የቶጎጫሌ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የቶጎጫሌ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት በቃ፡፡ በመርሃግሩ ላይ የተገኙት የሶማሌ ብሔራዊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ከለውጡ ወዲህ በክልሉ በተለያዩ የልማት መስኮች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ በመጠጥ ውሃ ዘርፍ ጅግጅጋ፣ ጎዴ ቶጎ ጫሌ የመሳስሉ ከተሞች ላይ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል፡፡ ክቡር ርዕስ መስተዳድሩ አክለውም ውሃ ላይ በተሰራ ስራ በክልሉ ድርቅን የመቋቋም አቅምን አሳድገናልም ብለዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅ መሠረታዊ ቢሆንም ዘላቂነቱን የሚያረጋግጡ ስራዎች ካልተሰሩ ተገቢውን ግልጋሎት ማግኘት አይቻልም ያሉ ሲሆን፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ፕሮጀክቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ እና አገልግሎቱ እንዲሳለጥ የውሃ አገልግሎት ተቋሙን የማስተዳደር አቅም በማጎልበት የበኩላችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ ብለዋል፡፡ ክቡር ሚንስትር ድኤታው አክለውም በፌደራል መንግስት ድጋፍ በክልሉ በተለያዩ ከተሞችና ወረዳዎች እየተገነቡ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የክልሉ ውሃ ቢሮ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከዚህ በፊት ከነበረው ክትትልና ድጋፍ የላቀ እንቅስቃሴ ብማድረግ ፕሮጀክቶቹን ውጤታማ እንዲያደርጉ አሳሰበዋል፡፡ በመድረኩ የኢነርጂ ሚንስትር ድኤታው ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሥልጣን ወሊም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ከ490 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የቶጎ ጫሌ ፕሮጀክት በቆላማ እና ውሃ አጠር አካባቢዎች የሚተገበረው የባለብዙ መንደር የሲአር ዋሽ (CRWASH)ፕሮጀክት አካል ሲሆን፤ ለ20 ዓመታት ዘላቂ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ ነው፡ የቶጎ ጫሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የግንባታ ስራውን የሶማሌ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት ያከናወነ ሲሆን፤ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን የሶማሌ ዲዛይንና ቁጥጥር ድርጅት አከናውኗል፡፡

Share this Post