በኢትዮጵያ ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት እንዲሰፍን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት እንዲሰፍን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ። ሚያዚያ 4/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ ) በኢትዮጵያ ዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት እንዲሰፍን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ተብሏል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማእከል ጋር በጋራ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን ተግባራዊ ከሚደረጉ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን የብራይት ፕሮጀክት በአምስት ዋና ዋና ተፋሰሶች በአባይ ፣ አዋሽ ፣ ኦሞጊቤ ፣ተከዜና ስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰሶች ላይ እየተገበረ ይገኛል። ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው አንዱ በሆነው የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ ይፋዊ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ያነጋገርናቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ብዙነህ አስፋው የብራይት ፕሮጀክት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን መሬት ላይ በማውረድ ዜጎችንና አካባቢን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚከሰቱ ችግሮች ተጋላጭነታቸውን በመቀነስ የንሮ ደረጃቸውን የማሻሻል ግብ ሰንቆ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱን በአምስቱ ተፋሰሶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉና ለተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ምቹ የሆኑ ሳይቶች ተመርጠው በመጠናቀቃቸው የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል የቀጣይ ተግባራችን ነው ብለዋል። የውሃ ሀብት አስተዳደር ቅንጅታዊ አሰራርን ይፈልጋል ያሉት አስተባባሪው እያንዳንዱ አካል በጋራ በመሆን ለፕሮጀክቱ ውጤታማነትና ዘላቂ ተጠቃሚነት ሊረባረብ ይገባል ፤ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል። ፕሮጀክቱ በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ ሲተገበር በተለያዩ ምክንያቶች ለውሃ ሀብት እጥረት ፣ ለብክለትና ለስነ ምህዳር መጎሳቆል መንስኤ የሆኑትን በመለየት መከላከልና የሚያደርሱትን ተጽእኖዎች መቀነስ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት ይሰራልም ብለዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛቴ ግጄ ፕሮጀክቱ በክልላችን መተግበሩ ትልቅ እድል በመሆኑ ከሚመለከታቸው ጋር ተቀናጅተን የሀሪ ተፋሰስ ምሰሳሌ ሊሆን በሚችል መልኩ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን ብለዋል። ተፈጥሮን መንከባከብና መጠበቅ ለዘላቂ የውሃ ሀብት አስተዳደር ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም አካል ለአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል። የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ም/ኃላፊና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አለይካ ሽኩር በበኩላቸው እንደ ክልል በርካታ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ ሲሆን ብራይት ፕሮጀክት በየአቅጣጫው የተጀመሩ ስራዎቻችንን ያሳልጥልናል ብለዋል። የውሃ ሀብታችን የሁሉም ነገር መነሻ በመሆኑ በተገቢው መንገድ መምራት፣ አቅሙን ማሳደግ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን መስራት ለነገ የማይባል ተግባር ነው ብለዋል ሀላፊዋ ። የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ ከተፋሰሶች ሁሉ በተለየ ሁኔታ ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ በሚያስችል አግባብ እየተሰራ ያለው ስራ ተስፋ ሰጭ ነውም ብለዋል። በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተግባራዊ የሚደረገው የብራይት ፕሮጀክትን ውጤታማት በሆነ መልኩ ለመፈጸም በየደረጃው ካሉ መዋቅሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ የመፈጸም አቅምን ማጎልበት ፣ በፕሮጀክቱ ትግበራ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን አስቀድሞ በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ መንደፍ እና ተያያዥ ጉዳዮችን መፈጸም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተመላክቷል።

Share this Post