የብራይት ፕሮጀክት በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ በይፉ ወደ ተግባር ሊገባ ነው።
ሚያዚያ 3/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት አስተዳደር ጋር በጋራ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማሳለጥ የሚያስችለውን የብራት ፕሮጀክት በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ በይፋ ወደ ተግባር ለማስገባት የሚያስችለውን የባለድርሻ አካላት ውይይት በአርባ ምንጭ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለውና ውስብስብ ችግሮቾ ያሉበትን የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ በተቀናጀ መልኩ ለመምራት ፣ለማስተዳደርና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር አካል በሆነው የብራይት ፕሮጀክት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
አላቂና ለአደጋ ተጋላጭ የሆነ የውሃ ሀብታችን በጋራ ለመጠበቅና ለመንከባከብ ፖለቲካል ቁርጠኝነት ይጠይቃል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ሀላፊነቶቻችን ወደ መሬት ለማውረድ ትልቅ መሳሪያ የሆነው የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለውሳኔ ቀርቧል ብለዋል።
በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መርሃ ግብር መሰረት ተቃኝቶ የቀረበው ብራይት ፕሮጀክት ታላሚ የሚያደርገውም የመፈጸም አቅምን ለመገንባት፣ የመረጃ ስርዓታችን የተሳለጠና ዘመናዊ ለማድረግ፣ ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው አምስቱ ተፋሰሶችን እቅድ ለማጠናቀቅና በሚገባ ለመተግበር ፣ ከውሃ ሀብት ጋር ተዛማጅ የሆኑትን በጋራ ለማየት እንዲሁም ተባብሮ የመስራት ተስፋ የምናይበት ነው ብለዋል።
መድረኩ የየድርሻችን ወስደን በመተግበር በቀጣይ ቆጥረን የምናስረክብበትና ተምክሮዎችን የምንቀምርበት እንዲሁም በሚገባ የምንገመግምበትን እድል የሚፈጥር በመሆኑ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ለፕሮጀክቱ ድጋፋ ላደረጉ የኒዘርላድስ መንግስትና የአውሮፓ ህብረት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በክቡር ሚኒስትሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የውሃና መሬት ሀብት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ ውብና ድንቅ ሀብት የያዘውን የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስን ስትራቴጅ ነድፎ ለመጠበቅ ፣ለመንከባከብና ለማልማት በብራይት ፕሮጀክት ይተገበራል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ አሳታፊ በሆነ መንገድ መተግበሩ ከዛላቂነት አኳያ ከፍተኛ ድርሻ አለው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህ ደግሞ ማእከላችን ያለውን ከፍተኛ ልምድ ተጠቅሞ ከዚህ አድርሶታል ብለዋል።
የውይይቱ አላማም ለውሳኔ ሰጭ አካላት ግንዛቤ በማስጨበጥ ፕሮጀክቱን ከላይ እስከታች ተናቦ ለመተግበር ያግዛል ብለዋል።
የባለድርሻ አካላት የባለቤትነት ስሜት ለዘላቂነት ወሳኝ በመሆኑ የምንከተለው አሳታፊ የትግበራ ስልት አጋዥ ስለሆነ በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል።
በመድረኩ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ክቡር ዶ/ር መስፍን መንዛን ጨምሮ ከደቡብ ኢትዮጵያ ፣ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከሲዳማ ክልል ፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዩችና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።