ክቡር ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ጋር ተወያዩ ፡፡
ሚያዝያ 01 /2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሰደር ሱን ክሮግስትሩፕ ጋር በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ትብብር ዙሪያ ተወያዩ፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ የዴንማርክ መንግስት በአቅም ግንባታ፣ በቴክንካዊ ድጋፍ እና በታዳሽ ኢነርጂ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ፤ በተለይም በንፋስ ኃይል ልማት ላይ በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በመጠጥ ውሃ ዘርፍ፤ በተለይ በቆላማ እና ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ላይ በሚተገበረው ፕሮግራም ላይ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል፡፡
የዴንማርክ አምባሰደር ሱን ክሮግስትሩፕ በበኩላቸው የዴንማርክ መንግስት በታዳሽ ኢነርጂ ልማት፣ በኤሌክሪፊኬሽን ላይ፤ በውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ እና በከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ላይ በትብብር እየተሰራ መሆኑን አንስተው፤ የአሰላ የነፋስ ሀይል ማመንጫ በታዳሽ ሃይል ልማት ላይ የሚደረገውን ትብብር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
አምባሳደሩ በማከል የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለመደገፍ የዋሽ ፕሮግራምን በተለየ አቀራረብ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚነስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው የዋሽ ፕሮግራም ላይ የሚደረገው ተሳትፎ በርካታ የውሃ አጠር አካባቢዎች ላይ የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡