በሶስቱ ተፋሰሶች የሚተገበረው የብራይት ፕሮጀክት በሙሉ አቅም ወደ ተግባር ሊገባ ነው።

በሶስቱ ተፋሰሶች የሚተገበረው የብራይት ፕሮጀክት በሙሉ አቅም ወደ ተግባር ሊገባ ነው። መጋቢት 30/2017ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) አዲስ አበባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ጋር በአባይ ፣ አዋሽና ተከዜ ተፋሰሶች የሚተገበረውን የብራይት ፕሮጀክት በሙሉ አቅም ወደተግባር ለማስገባት የሚያስችል የባለድርሻ አካላት ውይይት አድርጓል። በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ የብራይት ፕሮጀክት በሀገር ደረጃ የተዘጋጀውን የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር እቅድ በሚገባ ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል ነው ብለዋል። ብራይት ፕሮጀክት በ11ክልሎች በአምስት ተፋሰሶች በአባይ ፣ አዋሽ ፣ ተከዜ ፣ ኦሞ ጊቤና ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ ያለውን የውሃ መጠንን፣ ጥራትን እና አጠቃላይ የተፋሶችን መረጃ መሠብሰብ የሚያስችል የቤዚን ኢንፎርሜሽን ሲስተምን የሚተገብር እና አጠቃላይ ተፋሰሱን የመጠበቅ ፣ የመንከባከብና የማልማት ስራ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተቀናጀ መልኩ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር እና ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን የጋራ ፕላት ፎርም ተዘጋጅቶ በተቀናጀ መልኩ ተፋሰሳዊ ክልል ተፈጥሮ እየተገመገመ የሚመራበትን ስርዓት ተግባራዊ የሚያደርግ ነውም ብለዋል። ፕሮጀክቱ በአባይ ፣ አዋሽና ተከዜ ተፋሰሶች ላይ በጋራ ሲተገበር የጋራ ራእይ በመያዝ በተቀናጀ እቅድና በተቀናጀ አካሄድ በመምራት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ስለሚያስችል ነውም ብለዋል ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው። ስራውን በሚገባ ወደ መሬት ለማውረድ የባለድርሻ እና ፈጻሚ አካላት ቀጥተኛ ተሳትፎ እና ሀላፊነት ወሳኝ በመሆኑ በሚቀርቡ ሰነዶች ላይ የጠለቀ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አካል የሆነው የብራይት ፕሮጀክት ዘላቂነት ያለው ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አሳታፊ በሆነ መንገድ የሚተገበር ነው ብለዋል። ውይይቱ ለውሳኔ ሰጭ አካላት ግንዛቤ ለማስጨበጥና ፕሮጀክቱን ከላይ እስከታች ባለው መዋቅር ተናቦ ለመተግበር ያግዛልም ብለዋል። በውይይቱ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተወከሉ ፣ የአማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ትግራይና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዘዳንት ጽ/ቤት ተወካይ የተመረጡ ዞንና ወረዳ ሀላፊዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች ፣ የአባይና አዋሽ ተፋሰስ ጽ/ቤት ሀላፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን የፕሮጀክቱ ዝርዝር ይዘት፣ የአተገባበር ሂደት፣ የደረሠበት ደረጃና የወደፊት አካሄድን አስመልክቶ የተዘጋጁ ጽሁፎች በሙያተኞች ቀርበዋል። ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረትና በኒዘርላንድስ መንግስት የ45ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ለአምስት አመታት የሚተገበር ነው።

Share this Post