ተፋሰስን የእቅድ አሀድ አድርጎ መውሰድ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን መሰረታዊ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ተፋሰስን የእቅድ አሀድ አድርጎ መውሰድ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን መሰረታዊ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ህዳር16/2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ እየተዘጋጀ የሚገኘው የባሮ አኮቦ ቤዚን ፕላን የመጀመሪያ ሪፖርት ላይ ከኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡ መድረኩን በውይይት የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ እንዳሉት የውሃ ሀብታችንን ከማልማትና ከመጠቀም ባሻገር የውሃ ሀብት አስተዳደራችን የዘርፉን አለም አቀፍ ተሞክሮ በመውሰድ፤ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መምራት ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልጸው በሀገር ደረጃ በዘርፉ ላይ ያለው ተሞክሮ ጅምር በሚባል ደረጃ ቢሆንም በተለያዩ መንገዶች የሚገኙ ልምዶችን በማስፋት፣ ክፍተቶችን እንደመማሪያ በመውሰድ መስራት ከተቻለ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቅሰው፤ በውሃ ሀብት ፖሊሲ እንደተቀመጠው ለውሃ ሀብት አስተዳደር ተፋሰስን የእቅድ አሀድ አድርጎ መጠቀም መሰረታዊ በመሆኑ የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት ካላቸው ተፋሰሶች በተጨማሪ የኦሞ ጊቤ፣ የዋቢ ሸበሌና የገናሌ ዳዋ ተፋሰሶች ቤዝን ፕላን ዝግጅት በወላይታ ሶዶ፣ መደወላቡና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው የባሮ አኮቦ ተፋሰስ ቤዚን ፕላን በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ በኩል እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እየተከናወኑ ያሉ የቤዚን ፕላን እቅድ ዝግጅት ፕሮጀክት አፈጻጸም በጋራ እየተገመገመ እተየመራ መሆኑን ጠቅሰው የባሮ አኮቦ ቤዚን ፕላን ዝግጅትን በጥልቀት በመገምገም ውጤታማ ተግባር ለማከናወንና ለእቅዱ ስኬታማነት የ4ቱ ክልሎች ተሳትፎ በተለይም፤ የግብርና፣ የዉሃና የአካባቢ ጥበቃ ሴክተሮችን ማሳተፍ ለእቅዱ ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል፡፡ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ለታ ተስፋየ የተፋሰስ እቅድ ስራውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና የባሮ አኮቦ የተፋሰስ እቅድ ዝግጅትን በተሻለ ሁኔታ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና የተሰጣቸውን እድል በመጠቀም ከክልሎችና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተፋሰስ እቅድ ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት በመስራት የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት በተለይም በተፋሰሱ የውሃ ሀብት ጉዳይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚችል ስራ እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡ በዕቅዱ ላይ ተሳታፊዎች በርካታ ሃሳብ አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡ ከአስተያየቶቹ መካከልም ተየተነሱ በእቅዱ ቢካተቱ፣ ማስተካከያ ቢደረግባቸው እና የበለጠ ትኩረት ይሻሉ ያሏቸውን ነጥቦች እና አስተያየቶች እንዲሁም ግልጽ ያልሆኑና ጥያቄ የፈጠሩባቸውን ጉዳዮች ያነሱ ሲሆን በክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው የማጠቃለያ ሃሳብና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

Share this Post