በጣም ገጠራማ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
መጋቢት 30/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር በቡብ ምእራብ ዞን ሚኒት ሸሽ ወረዳ ይርን ቀበሌ የተገነባ የሶላር ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክት በተመረቀበት ወቅት በጣም ገጠራማ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ኤሌክትሪፍኬሽን ዘርፍ የአደሌ ፕሮጀክት እና የአፍሪካ ልማት ባንክ አስተባባሪ አቶ አዲስ ዓለም መብራቱ የኤሌክትሪ ፍኬሽን ዘርፍ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው በአፍሪካ ልማት ባንክ የገንዘብ ድጋፍ 25 ሚኒ ግሪድ ፕሮጀክቶችን በመገንባት በጣም ገጠራማ አካባቢ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹም በአብዛኛው በመጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ ፤ በቆላማ አካባቢ የሚኖሩና ከፊል አርብቶ አደር የሆኑ አካባቢዎች ወደኋላ እንዳይቀሩ ሀገሪቱ ካስቀመጠችው እቅድ አንጻር ፍትሀዊ የሀይል ተጠቃሚትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑ የይርኒ ሶላር ሚኒ ፕሮጀክት ማሳያ ነው ብለዋል።
በይርኒ ቀበሌ የተሠራው ፕሮጀክት 60ሚሊየን ብር የወጣበት እና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል የተተገበረ ሲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዋናነት ፕሮጀክቱን በማስተባበር ፣ በመምራትና በመከታተል ለፍጻሜ ማድረሱን ገልጸዋል።
የይርኒ ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ ወይንሸት ወርቁ በበኩላቸው መብራትን የምናውቀው በስም ወይም ከተማ ስንሄድ የነበረ ሲሆን ዛሬ ደጃችን ላይ በመምጣቱ ደስታችን ከቃላት በላይ በመሆኑ ላስታወሰን መንግስትና ሶላሩን ለሰሩልን ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
በዚህ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ በመረጃም ሆነ በሌላ ነገር እጅግ ወደኋላ የቀረ ነበር አሁን ላይ በዚህ ፕሮጀክት ከሌሎች እኩል ሆነናል፤ በተለይ ለሴቶች ብዙ ነገሮችን ይዞልን ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።
በቀጣይም ያለብን የውሃ ችግር እንደሚፈታልን ተስፋ አለን ያሉት ወ/ሮ ወይንሸት ባጠቃላይ ከአሁን በፊት ያላየነውን አይተናል ብለዋል።
አቶ ተሾመ አርትቴራች በበኩላቸው ስለ ፕሮጀክቱ ታሪክ የቀየረ በጨለማ የተገኘ ብርሀን በመሆኑ እንደ ግል ንብረታችን በመንከባከብ ጠብቀን እንደምንይዝ ለመግለጽ እወዳለሁ በማለት ፕሮጀክቱ ምን ያክል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።
ባጠቃላይ ምእራብ ኦሞ ዞን መኒት ሻሽ ወረዳ ይርኒ ቀበሌ የተገነባው የሶላር ፕሮጀክት 5 ሺ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግና ያሉባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ነው።