የአሞኒያ ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚደረገውን ጥረት አጋዥ የሆነ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
መጋቢት 26/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) አዲስ አበባ የአሞኒያ ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚደረገውን ጥረት አጋዥ የሆነ ስልጠና ለዘርፉ ሙያተኞች እየተሰጠ ነው፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጂአይዜድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የስልጠና መድረክ ያነጋገርናቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ሀብት ጥናት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሌብ ታደሰ ስልጠናው በሶስት ዙር የተሰጠ ሲሆን እንደሀገር የግሪን ሀይድሮጅን ቴክኖሎጅን በመጠቀም የአሞኒያ ማዳበሪያ በማምረት በምግብ ራሳችንን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እያዘጋጀ ላለው የግሪን ሀይድሮጅን ስትራቴጅም ግብዓት ለማሰባሰብ ፣ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ስትራቴጀው የጠነከረ እንዲሆን በየጊዜው የሚሰጡ ስልጠናዎችና የሚደረጉ ውይይቶች ወሳኝነት አላቸው ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር ያለንን የታዳሽ ሀብት በመጠቀም ክቡር ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ እንዳሉት የቀጣይ ህዳሴያችን የሆነውን ማዳበሪያን ለማምረት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙና ስራውን ወደ መሬት ለማውረድ አስተዋጽኦ ላላቸው አካላት የግሪን ሀይድሮጅን ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ቴክኖሎጅው አዲስ እንደ መሆኑ ለተግባራዊነቱ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ተቋምም ቁርጠኝነት ስላለ ሁሉም አካል ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ዘመቻ በመደገፍ ከጎናችን እንዲሆኑ ሲሉ አደራ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጀርመን ኢነርጂ ትብብር ፕሮጀክት ሀላፊ አቶ ሳምሶን ቶሎሳ አስካሁን በታዳሽ ኢነርጂ ያለማነው ከዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ጠቅሰው ይህንን የታዳሽ ሀብታችን ተጠቅመን ማዳበሪያ በማምረት በዓመት ለማዳበሪያ የሚወጣውን 1.3 ቢሊየን ዶላር በማስቀረት በአጭር ጊዜ ትርፋማ ከመሆን ባለፈ ለጎረቤት ሀገራም ማቅረብ የምንችልበት እድሉ ሰፊ ነው ብለዋል፡፡
ስራው ብዙ ማሰብና መወያየት የሚጠይቅ በመሆኑ ለመንግስትና ለግል ዘርፉ ብቻ የሚተው ሳይሆን እያንዳንዱ ባለሙያ ነኝ የሚል ዜጋ ፈቃደኛ ሆኖ ለተግባራዊነቱ አዋጽኦ ማድረግ አለበትም ብለዋል፡፡
የሀዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የአፈር ማይክሮ ባዮሎጂ ተመራማሪ የሆኑት ወ/ሮ ገነት ጌታቸው ስልጠናው እንደ ሀገር የግሪን አሞኒያ ማዳበሪያ ለማምረት ያለውን ምቹ ሁኔታና አቅም እንድንረዳ ከማድረጉ በላይ ከኬሚካል ማዳበሪያ ወጥተን ኦርጋኒክ ማዳበሪያን በማምረት ተጠቃሚ የምንሆንበትን እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ለጤና የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ስልጠናው በጀርመን ኤክስፐርቶች እየተሰጠ ሲሆን ከግብርና ፣ ከኢነርጂ፣ ከምርምር ተቋማት፣ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ የተውጣጡ የዘርፉ ሙያተኞች ስልጠናውን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡