"ትላንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና" በሚል መሪ ቃል ውይይት እየተካሄደ ነው።
መጋቢት 23/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች ከተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ጋር በመሆን "ትላንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና" በሚል መሪ ቃል ውይይት እያካሄዱ ነው።
በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ "የመጋቢት 24 ፍሬዎች እና ቀጣይ የሀገራችን ተስፋ" በሚል የተዘጋጀ ፅሁፍ ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት የዛሬ ሰባት አመት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ኢትዮጵያውያን ያነሱትን ጥያቄ ተቀብለው በራሳቸው ፍቃድና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ህዝቡ ወዶና ፈቅዶ በመረጠው እንድትመራ ስልጣን ያስረከቡበት ቀን በመሆኑ ዲሞክራሲን የተማርንበትን ዕለት እንዘክራለን ብለዋል።
ስልጣንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማስተላለፍ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ፤ መጋቢት 24 ባለፉት ሰባት አመታት ኢትዮጵያ በብዙ ውጣ ውረድ መካከል በለውጥ ጎዳና ውስጥ እንደነበረች የሚያስታውሰን በመሆኑ እንደተቋም እኛ ምን አሳካን፤ ምንስ ይቀረናል የሚለውን ለማየት ያስችላል ብለዋል።
መጋቢት 24ን ማክበር ያስፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ ሁሉም የተቋሙና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት በጋራ በመወያየት የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ በመድረኩ ላይ መጋቢት 24ን ላለፉት ሰባት አመታት ወደኋላ ስናስታውስ መላው የሀገራችን ህዝቦች ለውጡን የደገፉበትና ብልፅግናን እውን ለማድረግ በፓርላማ ፊት ቃል የተገባበት በመሆኑ ቀንኑ ማሰብ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርና እንደተቋም ያስመዘገብናቸውን ድሎች ዕውቅና በመስጠት፤ ብልፅግናችንን ለማስቀጠል ቃል የምንገባበት መድረክ ነው ብለዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የተጀመረ ሲሆን፤ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት፣ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ስራተኞች እየተሳተፉበት ይገኛል።