በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተገነቡና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑ ተገለጸ።
መጋቢት/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተገነቡና በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ጥሩ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ እንዳሉት ባለፉት ሶስት አመታት በልዩ ትኩረት በአፉር በሱማሌ እና ቦረና ዞን በሲአር ዋሽና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክቶች በርካታ የውሃ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ከሰሞኑ በቦረና ዞን በከፍተኛ አመራሩ የተደረገው የመስክ ምልከታ ስኬት ያየንበት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የሚጤ፣ ሮምሶና ኤርደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አገልግሎት መስጠት ችለዋል ብለዋል።
እንደ ዞን 72 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን 1000 ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው 4 ሪዘርቬየሮች ያሉት ፕሮጀክት የመስመር ዝርጋታ ስራ እየተሠራ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሳይጠናቀቅ ከስር ከስር ህብረተሠቡ ውሃ እያገኘ የሚሄድበት አሰራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየተደረገ ነውም ብለዋል።
በዞኑ ስድስት ወረዳዎች እየተተገበሩ ባሉ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ክፍተት የታየባቸው ተገምግመው አቅጣጫ በማስቀመጥ መታረም የሚገባቸው ላይ የርምት እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በስድስት ወር የፕሮጀክቶች አፈጻጸምም 1.5 ሚሊየን የህብረተሰብ ክፍል የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል።
በግድቤን በደጄ ፕሮጀክትም በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትና በአርብቶ አደር አካባቢዎች በሁለት አመታት ጊዜ ከ200 በላይ የመጠጥ ውሃዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የተረጋጋ የመማር ማስተማር ስርዓት እንዲሰፍን እና የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራምን እንዲሳለጥ ያደርጋል።
እናቶች ለህክምና ሲሄዱ በውሃ እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን የአገልግሎት መጓደል በማስቀረት እና ለሌሉች አገልግሎቶች በመዋል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያበረከተ ነውም ብለዋል።
በቀጣም የክልሎችን አቅም በማጎልበት በራሳቸው አቅም እንዲተገብሩት ለማስቻል እየተሰራ እንደሆነ ክቡር ሚኒስትሩ አክለዋል።