የውሃ ሀብታችንን በመጠበቅ ፣ በመንከባከብ እና በማልማት ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚጠበቅ ተገለጸ።
መጋቢት 13/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) አዲስ አበባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአለም የውሃ ቀንን ባከበረበት መድረክ የውሃ ሀብታችንን በመጠበቅ ፣ በመንከባከብ እና በማልማት ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
በአሉን አስመልክቶ በነበረው የፖናል ውይይት የዘርፉ ምሁራን እንዳሉት የውሃ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የምንተክላቸው ዛፎች በተለይም በተፋሰሶች አካባቢ የሚተከሉት ውሃን በብዛት የሚጠቀሙ እንዳይሆኑ ባለፉት ስድስት አመታት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ስራዎቻችን ላይ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ባለፉት ስድስት አመታት በአባይ ተፋሰስ ብቻ የተተከሉት 11 ቢሊየን ዛፎች ውሃን የሚያበለጽጉ መሆናቸው ማሳያ ነው ተብሏል።
ውሃን በአግባቡ ይዘን ካልተጠቀምንበት የሚመጣው አደጋ የከፋ ሊሆን እንደሚችልም ነው የተጠቆመው።
በተለይም የከርሰምድር የውሃ ሀብት ላይ ያለውን ተጽእኖ በሚገባ ማየትና የበለጠ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።
እንደነዚህ አይነት ስራዎች ሲሰሩ ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ፣ በምርምር የታገዘ እንዲሁም በትብብር ሊሆን እንደሚገባም ነው የተገለጸው ።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን በመጠበቅ ፣ በመንከባከብና በማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በአረንጓዴ አሻራ ልማት የምትሰራቸው ስራዎች ለአለምም የአየር ንብረት መዛባትን፣ ጎርፍንና ደለልን በመቀነስ እንዲሁም ድርቅን በመከላከል ረገድ ጠቀሜታቸው የጎላ በመሆኑ አለም አቀፍ ትብብር አስፈላጊ ነውም ተብሏል።
ህዳሴ ሲገደብ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጎርፍንና ደለልን በመቀነስ አመቱን ሙሉ የውሃ ፍሰቱ ሳይቀንስ ጥቅም እንዲሰጥ መደረጉ ማሳያ ነውም ተብሏል።
ስለሆነም በውሃ ላይ የተሰራውን ጠንካራ ስራ ጠቀሜታውን እንዲረዱ የማሳመን ስራ በመስራት ወደ ትብብር ገብተው የተሰራውን ስራ እንዲደግፉ ማድረግ ይገባልም ተብሏል።
በውይይቱም በርካታ ጠቃሚና ገንቢ አስተያየቶች እንዲሁም ጥያቄዎች በተሳታፊዎች ተንጸባርቀዋል።