''የውሃ ጥበቃን መረዳትና ማጎልበት" በሚል መሪ ቃል የአለም ውሃ ቀን እየተከበረ ነው።

''የውሃ ጥበቃን መረዳትና ማጎልበት" በሚል መሪ ቃል የአለም ውሃ ቀን እየተከበረ ነው ። መጋቢት 13/2017ዓ.ም (ው .ኢ.ሚ) አዲስ አበባ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አለም አቀፍ የውሃ ቀንን ''የውሃ ጥበቃን መረዳትና ማጎልበት'' በሚል መሪቃል እያከበረ ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ማርች 22 በኢትዮጵያ ደግሞ መጋቢት 13 የሚከበረው የአለም የውሃ ቀንን ስናከብር ውሃ ሀብትን በተመለከተ ልንገነዘባቸውና ትኩረት ልናደርግባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበዓሉ መክፈቻ ላይ ተናግረዋል። ክቡር ሚኒስትሩ ውሃ ህይወት ነው! ህይወቱን ጠብቆ እንዲኖርና ተጠቃሚነታችን እንዲረጋገጥ በየቤታችን ለምንጠቀመው ውሃም ተገቢውን ጥንቃቄና እንክብካቤ ማድረግ አለብን ብለዋል። እንደ ሀገር የውሃ ሀብት ደህንነት ጥበቃ ስራችን በአረንጓዴ አሻራ ልማታችን እውን ሆኗል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ለዚህ ደግሞ ከእኛ አልፎ ለአለምም የሚጠቅም ስራ ሰርተናል ብለዋል። አለምአቀፍ የውሃ ቀንን ስናከብርም የውሃ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ትኩረት እንዲሰጠው ታሳቢ በማድረግም ነው ብለዋል። እንደሀገር ''የውሃ ማማ'' እየተባልን ለድርቅና ለውሃ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መኖራቸውን አንስተው፤ የውሃ ሀብታችን በአግባቡ በመጠበቅና በመንከባከብ የበለጠ ተጠቃሚነታችን ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል። የውሃና ኢነርጂ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በአሉን ለማክበር ታድመዋል።

Share this Post