ለኦሞ ጊቤ ቤዚን ፕላን ተግባራዊነት ቤዚኑን የሚጋሩ ክልሎችና ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ።
መጋቢት 12/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) "የተፋሰስ አስተዳደር ድጋፍ ለጠንካራ፣ አካታችና ተስማሚ ለውጥ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የውሃ ሀብት አስተዳደር" በሚል ፕሮግራም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ጋር በጋራ ባዘጋጀው ይፋዊ የኦሞ ጊቤ ቤዚን ማስጀመሪያ መድረክ ላይ ለኦሞ ጊቤ ቤዚን ፕላን ተግባራዊነት ቤዚኑን የሚጋሩ ክልሎችና ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ።
የኦሞ ጊቤ ቤዚን ይፋዊ ማስጀመሪያ መድረኩን የመሩት የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ በቀጣይ አምስት አመታት የሚተገበረው ፕሮጀክት በተናጠል የሚመራ ከሆነ የፍትሃዊነት ችግርን ስለማይፈታ በቀጣይ ከውሃ ሀብት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚሰሩ ተቋማትን አቅም በማጎልበት ዕቅዳቸውን ከፕሮጀክቱ ጋር አጣምረው እንዲያዘጋጁ ለማድረግ እንዲሁም ፕሮጀክቱ የኦሞ ጊቤ ቤዚንን በስኬት ለመተግበር ቅንጅታዊ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፕሮጀክቱ በአውሮፓ ህብረት (EU) እና በኔዘርላንድ ኪንግደም ኤምባሲ (EKN) የገንዘብ ድጋፍ፤ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና በውሃና መሬት ልማት ማዕከል የሚተገበረው የኦሞ ጊቤ ቤዚን፣ የአባይ፣ የአዋሽ፣ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች እና የተከዜ ቤዚኖች ላይ ተግባራዊ በሚደረገው ስራም በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ የዘላቂ ልማት ግቦችን (SDG) ለማሳካት የሚያስችሉ የተቀናጀና የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ ሀብት አስተዳደር የመፍትሔ አማራጮችን ማቅረብ ላይ በትኩረት የሚሰራ ነው።
በስድስት ወርክፓኬጅ የተደራጀ ፅሁፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ለተሰጡት አስተያየትና ለተነሱ ጥያቄዎች ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ እና ዶ/ር ጌቴ ዘለቀ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።