ክቡር ሚኒትሩ ከፊላንድ ልኡካን ቡድን ጋር ተወያዩ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ፣ የመካለኛው ምስራቅና የላቲን ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር በአምባሳደር ሄሌና ኤራክሲነን ከተመራ የፊላንድ ልኡካን ቡድን ጋር ተወያዩ።
ኢትዮጵያና ፊላንድ በውሃው ዘርፍ በሚያደርጉት ትብብር ላይ ትኩረት አድርጎ በተካሄደው ውይይት ላይ ክቡር ሚኒስትሩ የፊላንድ መንግስትና ህዝብ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀው የፊላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር የሚተገብረው አምስተኛው ዙር የኮዋሽ ፕሮግራም ሊያካሂዳቸው የሚገቡ ማሻሻያዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ውሃ አጠርና ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎች ላይ፤ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸው የመጠጥ ውሃ መሰረተልማቶች የሚገኙበት አካባቢዎች ላይ፤ በጸሀይ ሀይል የሚሰራ የውሃ መሰረተ ልማት መገንባት ላይ፤ የውሃ አገልግሎቶችና የዋሽ ኮሚቴዎች ላይ የአቅም ግንባታ ስራች ላይና የውሃ ሀብት መረጃ ስርዓት ማዘመን ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት በሚያስችል መልኩ መተግበር እንደሚገባው ገልጸዋል።
በፊንላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ የመካለኛው ምስራቅና የላቲን ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሄሌና ኤራክሲነን አመስተኛውን ዙር የኮዋሽ ፕሮግራም አተገባርን በተመለከተ በቀጣይ ውይይቶችን በማድረግ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ አስረድተዋል፡፡