የባዘርኔት ፕሮጀክትን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ሀይድሮሎጅካል ሞዴሊግ ተግባራዊ ሊሆን ነው።
መጋቢት 10/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጣሊያን መንግስት የልማት ትብብር ድርጅት ጋር በጋራ የሚተገብረውን የባዘርኔት ፕሮጀክት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ሀይድሮሎጅካል ሞዴሊግ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።
በCIMA (ሲማ) ፋውንዴሽን የምርምር ድርጅት ተዘጋጅቶ የቀረበው የሀይድሮሎጅካል ሞዴሊግ ሲስተም በባዘርኔት ፕሮጀክት የሚሰራው ስራ የተሳለጠ እንዲሆን ያስችላል ሲሉ የአውሮፖ ህብረት ፕሮግራም ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ማርኮ ላንዲ በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ ገልጸዋል።
ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በተለያዩ ፕሮጀክቶች ለረጅም ጊዜ ሰርተናል ያሉት ዶ/ር ማርኮ በሶስቱ ተፋሰሶች ማለትም በአዋሽ፣ ዋቢሸበሌ እና ደናክል ተፉሰሶች ላይ የሚሰራውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ የጣሊያን መንግስት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተገበረ የሚገኘው የባዘርኔት ፕላስ ፕሮጀክት አካል የሆነው የሀይድሮሎጂ ሞዴሊግ ሲስተም በቀጣይ በሶስቱ ተፋሰሶች ለሚሰራው የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ፣ የውሃ ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም እና አሰሳ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
ሞዴሊጉ እንደ ሀገር ያለውን የተፋሰስ የዉሃ ሀብት ፣ የቅደመ ጎርፍ መከላከል ትንበያ እንዲሁም የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን በሚሰራው ስራ የሚታየውን የመረጃ ክፍተትም ይሞላል ብለዋል።
የሲምዚየሙ ዋና ዓላማም በቀረበው ሞዴሊግ ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ከመጡ የዘርፉ ሙያተኞች ግብአት በማሰባሠብ ውጤታማ ስራ ለመስራት ታላሚ ያደረገ ነው ብለዋል።
በሲምፖዚየሙ ዶ/ር ፍራንቸስኮ ፓንዚያኒ የሲማ (CIMA) ድርጅት ስለሚሰራቸውና እየሠራ ስላለው ዝርዝር መረጃ ያቀረቡ ሲሆን ዶ/ር አንድሪያስ ላይበርሰዲኖ ደግሞ ኦፕሬሽናል ሀይድሮሎጅካል ሞዴሊግን አስመልክቶ፤ እንዲሁም ዶ/ር ኒኮላ ባቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሁፎች ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሲምፖዚየሙ የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዘርፉ ሙያቸኞች ተሳትፈዋል።