የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን የሚያስችሉ የህግ ማእቀፎች መዘጋጀታቸው ተገለጸ፡፡

የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን የሚያስችሉ የህግ ማእቀፎች መዘጋጀታቸው ተገለጸ፡፡ መጋቢት/2017ዓ.ም (ው. ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን የሚያስችሉ የህግ ማእቀፎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴታው ገለጻ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በቂ የዝናብ መጠን፤ በርካታ ወንዞችና ሀይቆች እዲሁም ሌሎች የውሃ አካላት ቢኖሯትም የዝናብ መጠኑ በቦታና በጊዜ ያለው ስርጭት የተዛባ በመሆኑ፤ በተፈጥሮ ሀብት መራቆት፤ በአየር ንብረት ለውጥና ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመጣው የህዝብ ቁጥርና ፍላጎት የተነሳ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም ብለዋል፡፡ ለእነዚህ ውስብስብ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ውሃን ማዕከል ያደረገ የተቀናጀ የባለድርሻ አካላት እቅድ፣ አሳታፊና ፍትሃዊ የውሃ ሀብት ምደባና አጠቃቀም ፈቃድ፣ ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት፣ ውጤታማ የባለድርሻ አካላት ትስስር መፍጠር ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንዳለና የውሃ ሀብት አስተዳርን ሊያሳልጡ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎችም ተዘጋጅተው መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ የመድረኩ ዋና ዓላማም የውሃ፤ መስኖ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው በተዘጋጁት የህግ ማዕቀፎች ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ አግኝቶ ድጋፍ ማድረግ እንዲችል ታላሚ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፈትያ አህመድ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ በተዘጋጁት የህግ ማዕቀፎች ላይ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር ከዚህ በፊት ከነበረን ግንዛቤ ላይ እውቀት የሚጨምር በመሆኑ ግንዛቤ ላይ የተመሰረተ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ይረዳናል ብለዋል፡፡ ውሃ የሀገሪቱ የልማት ማዕከል እንደመሆኑ የውሃ ሀብት አስተዳደር የህግ ማዕቀፎችን ወደ ተግባር ለመቀየር የብዙ አካላትን ድርሻ ስለሚጠይቅ ለሌሎች ሴክተሮችና ለክልሎች በበቂ ሁኔታ ማስገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል ፡፡ በእለቱም የውሃ አካል ዳርቻ ርቀት አወሳሰን፣ ልማት እና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጅ፣ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ረቂቅ አዋጅ፣ የውሃ ታሪፍ ደንብ እና በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የቀረቡ ሲሆን ከውሃ ፣መስኖ ቆላማ አካባቢና የአካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

Share this Post