“የዓባይ ግድብ እና ዓድዋ የአንድነታችን ማሰሪያ የቁጭታችንም ማሳያ ስኬቶቻችን ናቸው” –
ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር
ዓባይ ግድብ እና ዓድዋ ድል የአንድነታችን ማሰሪያ፤ የቁጭታችንም ማሳያ ስኬቶቻችን ናቸው ሲሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ:: ሁለቱም ስኬቶች በሕዝቡ እና በመሪዎች ቅብብሎሽ የተገኙ ድሎች መሆናቸውን አስታወቁ::
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳስታወቁት፤ የዓባይ ግድብም ሆነ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን አንድነት የተረጋገጠባቸው ስኬቶች ናቸው:: ኢትዮጵያውያውን በሁለቱም ላይ አንድነታቸውን አሳይተዋል፤ በቁጭት በሠሩት ሥራ የማይደፈር ማንነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል::
ሁለቱም ታላላቅ ስኬቶች ኢትዮጵያውያን በብቃት የተጫወትንባቸው ሜዳዎች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ጠላትን በዝረራ ከጨዋታ ወጪ ያደረግንበትን ድልም አስመዝግበንበታል ብለዋል:: ዓባይ ግድብ ሆነ ዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ይደርስባት የነበረውን የውጭውን ጫና በብቃት የመከተችበት ሲሆን፤ ያንን የተሳሳተ አስተሳሰብ ያኮላሸችበት ስኬቷ እንደሆኑም ገልጸዋል::
እንደ ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ዓድዋ ድል እና ዓባይ ግድብ የኢትዮጵያውያን አንድነት የተረጋገጠባቸው ናቸው:: ዓድዋ ላይ እንደ አሁኑ ጊዜ ቴክኖሎጂ አልነበረም::
ተንቀሳቃሽ ስልኩ፣ ኢንተርኔቱ እና ሌላ ሌላው አልነበረም::
እንዲያም ሆኖ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲባል ከጥግ ጥግ ድረስ በአራቱም ማዕዘን ንቅናቄ በመፍጠር ኢትዮጵያ የእኔ ናት ብሎ ስለሚያምን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሕዝቡ መንቀሳቀስ ችሏል:: በወቅቱ የራሱ የሆነና እንዲፈታለት የሚፈለገው ችግር ሊኖርበት ይችል ይሆናል:: ነገር ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ድርድር አያውቁም:: የዓባይ ግድብም በተመሳሳይ የሚጠቀስ ነው::
የዓባይ ግድብ በየትኛውም ክልል ሆኖ የትኛውም ቀበሌ ውስጥ ያለ ሰው ዓባይ ሲባል አንዳች የአንድነት እና የመተባበር መንፈስ ውስጡ እንዳለ ይታወቀዋል:: የእኔነት ስሜቱ የጎላ ነው:: ምክንያቱም ከሌለው ነገር ላይ ለዓባይ ግድብ አቋድሷል::
በዓድዋ በኩል ወይ ራሱ አሊያም ልጆቹን ወደ ግንባር እንዳላከ ሁሉ ለዓባይ ግድብም እንዲሁ በጉልበቱ፣ በገንዘቡና በሀብቱ ተሳትፏል:: ከዚህ መነሻነትም ዓድዋ ድልና ዓባይ ግድብ የአንድነት ማሳያ ናቸው:: ሁለቱም የኢትዮጵያውያን ምልክት ናቸው::
ሚኒስትሩ፣ ሁለቱም የውጭ ጫና የፈተናቸው ታላላቅ ስኬቶች ናቸው:: ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ጊዜ የተዋጋችው አንድን ሀገር ብቻ አይደለም:: በወቅቱ ከጣሊያን ጋር ኅብረት ከፈጠሩትና የቅኝ ግዛትን ማስፋፋት ከሚፈልጉት ሀገራት ጋር ሁሉ ነበር ማለት ይቻላል:: ኢትዮጵያ በወቅቱ ያሸነፈችው የተነሱባትን ኃይሎች ሁሉ ነው:: ይህ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል::
የዓባይ ግድብን በተመለከተ ደግሞ እኛን ስትገዳደረን የነበረችው ግብጽ ብቻ አይደለችም ያሉት ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ማሸነፍ የቻለችው በድህነቷ እንድትዘልቅ የሚፈልጉ ኃይሎችን ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል::
ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ምክንያት በጸጥታው ምክር ቤት ስትወሰድ ዓላማው ኢትዮጵያን በዚያ ደረጃ ማብጠልጠል ነው:: በመሆኑም በኢትዮጵያ ጥንካሬ እሱን ወደ አፍሪካ ኅብረት መመለስ መቻል ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን አመልክተዋል::
በዓድዋ ጊዜ በውጊያ የነበረው የቅኝ መግዛት ሕልም ኢትዮጵያ እንዳጨናገፈች ሁሉ አሁን ደግሞ በኢኮኖሚው በኩል በቅኝ ለመግዛት የተቋመጠውን አካሔድ ኢትዮጵያ ያሸመደመደችው መሆኑ ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ጉዳይ ነው ብለዋል::
እርሳቸው እንዳሉት፤ በጣም ወሳኙ ጉዳይ በኢትዮጵያ የውሃ ልማት ታሪክ ዛሬ ያመጣነው ስኬት በአንድ ጀምበር የመጣ ሳይሆን በትውልድ ቅብብሎሽ የተገኘ ስኬት ነው:: በዚህ ስኬት ውስጥ የመሪዎች ቅብብሎሽ አለ:: ንጉሱ አጼ ኃይለስላሴ የአሜሪካ ኩባንያ ቀጥረው ኢትዮጵያ ውስጥ ለግድብ የሚሆን ብዙ ቦታ ካስጠኑ በኋላ ብድር ጠይቀው ተከልክለዋል:: ይሁንና አንድ ቀን ኢትዮጵያውያኑ እንደሚገነቡት ተስፋ አድርገው አልፈዋል::