የ"ግድቤን በደጄ" ፕሮጀክት ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡

የ"ግድቤን በደጄ" ፕሮጀክት ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡

ህዳር 6/2015ዓ.ም (ውኢሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተቋሙ መካከለኛ አመራሮች ጋር የ"ግድቤን በደጄ" (የጣራ ላይ ውሃ ማሰባሰብ) ፕሮጀክት አጠቃላይ አፈጻጸም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡

የ"ግድቤን በደጄ" ፕሮጀክት አነሳሽ የሆኑት ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በቦረና ዞንና በጎንደር የተመረጡ ቦታዎች ተተግብሮ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን በነጻ የተሰጠንን ትልቅ የውሃ ሀብታችን በማሰባሰብ በተለይም ሴቶች ርቀው ሳይሄዱ በደጃቸው ውሃ የሚያገኙበትን እድል የፈጠረ ነው ብለዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሃሳቡን ወደ ተግባር በመቀየር ሰርቶ ማሳየት የተቻለበትን ሁኔታ ጠቅሰው በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንዲደረግ ትልቅ ጥረት የሚጠይቅ ስለሆነ መካከለኛ አመራሩም ይህንን ተረድቶ የሚጠበቅበትን ሁሉ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በዚህ ዓመት ፕሮጀክቱን በሚጠበቀው ልክ መሬት ላይ የማውረድ ስራ ተሰርቶ ህብረተሰቡ ተቀብሎ የሚተገብርበት ስርዓት እንደሚፈጠርና ኢትዮጵያውያን በራሳችን አቅም እና ጥረት ለውጥ የምናመጣበት ፕሮጀክት መሆኑንም አበክረው አስረድተዋል፡፡

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በበኩላቸው የክረምት ዉሃ በህብረተሰቡ ደጅ እያለፈ፤ አንዳንዴም ጉዳቶችን እያስከተለ ያለበትን ሁኔታ ጠቅሰው ይህንን የውሃ ሀብታችን በማሰባሰብ ተጠቃሚ የምንሆንበት እድሉ ሰፊ በመሆኑ ልክ ህንድን በመሳሰሉ ሀገሮች እንደሚተገበረው እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ የራሱን ዉሃ የሚያሰባስብበትና ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል በሰፊው የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጅ እንደሆነና በፖሊሲ ተካቶ መተግበር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ በቦረናና ጎንደር የተሰሩ ፓይለት ፕሮጀክቶች (የጣራ ላይ ውሃ ማሰባሰብ ፕሮጀክት) በትክክልም የህብረተሰቡን የውሃ ችግር ፈች መሆናቸውን ጠቅሰው በተለያዩ ወረዳዎች ላይ የጣራ ላይ ውሃ ማሰባሰብ እንደሚቻልና በቀላል ወጭ በርካታ ጥቅም እንደሚያስገኝ በጥናት አስደግፈው አቅርበዋል፡፡

Share this Post