የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት አዲሱን የጀርመን አምባሳደር ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት አዲሱን የጀርመን አምባሳደር ተቀብለው አነጋገሩ፡፡ ጥር 05/05/2017 ዓ.ም. (ው.ኢሚ.) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት አዲሱን የጀርመን አምባሳደር ሚ/ር ሀንስ ሀንፊልድን ተቀብለው አነጋገሩ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ንጹህ አረንጓዴ ኢነርጂ በማምረት፤ ቀጠናውን በሃይል ለማተሳሰር እየሰራች መሆኑን አንስተው፤ እየተከናወነ የሚገኘው ምስራቅ አፍሪካን በሃየል የማስተሳሰር ተግባር ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ከ74 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ የናይል ወንዝን ውሃ ሀብት በትብብር ከመጠቀም አንጻር የትብብር ማእቀፍ ስምምነቱ በስድስት ሀገራት መጽደቁ ሁሉኑም የተፋሰሱን ሀገራት ያካተተ የውሃ ትብብር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡ የጀርመን መንግስት በኢነርጂ ልማት ዘርፍ፤ በንጹህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦትና በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ድጋፍ እንደሚያርግ ጠቅሰው፤ በተለይ ጂአይዜድ በገጠር የሀገሪቱ ክፍል ኤሌኬትሪክ ለማዳረስ ለረጅም ጊዜ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ክቡር ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ከዋና የሀይል መስመር ርቀው የሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎችን የኦፍግሪድ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ አምባሳደር የንስ ሃንፊልድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በታዳሽ ሀይል ልማት ላይ ጥሩ እየሰራች መሆኑን አንስተው፤ የቀጠናዊ የሀይል ትስስሩ ዘርፈብዙ ትብበርን እንደሚያመጣ ጠቁመዋል፡፡ አምባሳደር የንስ ሀንፊልድ አክለውም በኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

Share this Post