የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የግድብ ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅ የሀብት ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር አካሄደ፡፡
ጥር 03/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የግድቡ ቀሪ ስራዎች ለማጠናቀቅ ለባንኮች ፣ ኢንሹራንሶች እና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተዘጋጀ የሀብት ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል አካሄደ፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት አፈፃጸም የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ኢትየጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያላሰለሰ ድጋፍ ማድረጋቸውን በመግለጽ በዚህ የንቅናቄ መድረክ ተሳታፊዎች የህዳሴ ግድብ ቦንድ ገዝተው የማያውቁ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ በማድረግ እስከ 60 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ፣ ከዚህ ቀድም ቦንድ ገዝተው የመመለሻ ጊዜው የደረሰ ቦንድ ያላቸው ደግሞ በድጋሚ እንዲያድሱ እንዲያደርጉ በማድረግ እሰከ 50 ሚሊዮን ብር በመሰብሰብ በድምሩ 110 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በማከል በሀብት ማሰባሰብ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ባንኮች ፣ ኢንሹራንሶች እና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን አመስግነዋል፡፡
በሌላ በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የፕሮጀክቱ ጥቅል አፈጻጸም 97 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን ገልጸው አሁን ላይ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የቀሪ ስራዎች ግብዓቶች ዘመናዊ፣ ጥራት ያላቸው ከውጪ ሀገር የሚገቡ ግብዓች እና የቴክኒክ ስራዎች ሲሆኑ፤ የውጪ ምንዛሬ የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ የሀብት ማሰባሰብ ንቅናቄ ስራዎች እና የድጋፍ ተሳትፎ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ደረጃ ላይ ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ የሆነውን ሀብት ለማሰባሰብ ይቻል ዘንድ የፋይናንስ ተቋማት ማለትም ባንኮችን፣ ኢንሽራንሶችን እና ማይክሮ ፋይናንሶችን ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ይፋ ተደርጓል፡፡
በገቢ ማሰበሳብ ንቅናቄው ላይ የ32 ባንኮች የቦርድ ሰብሳቢ እና የባንኩ ፕሬዘዳንቶች፣ የ18 ኢንሹራንሶች የቦርድ ሰብሳቢ እና የኢንሹራንስ ፕሬዘዳንቶች፣ የ34 ማይክሮፋይናንስ የቦርድ ሰብሳቢ እና ፕሬዘዳንቶች፣ ሚዲያዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡