የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ እና የውሃ አካል ዳርቻ ርቀት አወሳሰን፣ ልማት እና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጆች ላይ ውይይት ተካሄደ።
ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን በተፋሰሶች ለማረጋገጥ ታሳቢ ተደርገው በተዘጋጁት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ እና የውሃ አካል ዳርቻ ርቀት አወሳሰን፣ ልማት እና እንክብካቤ ረቂቅ አዋጆች ላይ ውይይት አካሄደ።
መርሀ ግብሩን ያስጀመሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ኢትዮጵያ ያሏትን የውሃ ሃብቶች በአግባቡ ለመጠቀም በምታደርገው ጥረት ውስጥ የውሃ አካላት በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰባቸውና የውሃ አካላቱ እየተበከሉ መጠናቸውም እየቀነሰ እንደሆነ አውስተው፤ አሁን ላይ ወቅቱን የዋጀ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ ያለንን ውስን ሀብት ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም ረቂቅ አዋጆቹ አስፈላጊ መሆናቸውንና ሁሉም ተሳታፊ ሀሳብ ሊሠጥበት ይገባል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ በርካታ ለውጦች እንዳሉ ገልጸው፤ ሀገራችን በቂ የዝናብ መጠን፣ በርካታ ወንዞች፣ ሀይቆችና ሌሎች የውሃ አካላት ያላት ቢሆንም በአየር ንብረት ለውጥ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የህዝብ ቁጥርና እያደገ በመጣው ፍላጎት የተነሳ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ብለዋል።
እየገጠሙ ላሉ ተግዳሮቶች መፍትሄ ለመስጠት ውሃን ማእከል አድርገው ለሚከናወኑ የልማት ተግባራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት እቅድና ትግበራ እንዲኖር፤ ክትትል በአግባቡ እንዲከናወን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ሁሉም የውሃ ተጠቃሚ በፈቃድ ላይ የተመሠረተ አጠቃቀምን በመረዳትና በመተግበር የውሃ ሀብታችን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ግጭቶች ፣ የውሃ ብክለትና ብክነትን መከላከል ጊዜው የሚጠይቀው ተግባር ነው ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትሩ በማያያዝ ተሳታፊዎች በሚቀርቡት ጹሁፎች ላይ የራሳችሁን እውቀትና ልምድ በመጨመር በውሃና ተዛማጅ ሀብቶች ተጠቃሚ ያልሆነውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው፤ እነዚህን የህግ ማእቀፎች ለዚህ ደረጃ ለማድረስ ድጋፍ ላደረጉ የጠ/ሚር ጽ/ቤት ህግ ክፍልና ፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም ለተሳተፋ ሁሉ ምስጋና አቀርበዋል።
በሕ/ተ/ም የውሃ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈቲያ አህመድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሀገሪቱ ውሃ ሀብት አስተዳዳሪ በመሆኑ ልዩ ልዩ የህግ ማእቀፍ ማዘጋጀት ዋና ተግባሩ ነው ብለዋል።
ይህን ታሳቢ በማድረግ በፌደራልና ክልል በልዩ ልዩ ዘርፎች የተናበበና የተሳለጠ ልማት እንዲኖር ውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችል ማስፈጸሚያ የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት አዋጅ መዘጋጀቱ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ በሁሉም ቦታ ተደራሽ እንዲሆንና ውሃን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ መጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው በረቂቁ ላይ ተወያይቶ በተያዘለት የጊዜ ገደብ በማስረከብ ሀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ጽንሰ ሀሳብና የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት አስፈላጊነት፤ የውሃ አካል ዳርቻ ርቀት አወሳሰን፣ ልማትና እንክብካቤ ምንነት ላይ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢዎች፤ እንዲሁም የምክር ቤት አባላትና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።