የተቆጣጣሪ ባለስልጣን ማቋቋም ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲሸጋገር አቅጣጫ ተቀመጠ፡፡
ታህሳስ 02/2017 ዓ/ም የከተማ ውሃ አቅርቦት እና ሳኒቴሽን አገልግሎት የተቆጣጣሪ ባለስልጣን ማቋቋም ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲሸጋገር አቅጣጫ ተሰጠ።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክብር ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ እስከአሁን የመጣንበት የውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት እና አገልግሎት ውስንነቶች በዘላቂነት ለመፍታት ባለመቻሉ የከተማ የውሃና ሳኒቴሽን ተቆጣጣሪ አካል ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ታምኖበታል ብለዋል።
ተቋሙን ለማቋቋም ጥናት ያቀረቡት አማካሪዎች እና ያስተባበሩት የሚኒስቴሩ የስራ ኃላፊዎችን አመስግነው፤ ቀሪውን ሥራዎች በመጠናቀቅ ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲያሸጋግሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የከተማ ውሃ አቅርቦት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አዜብ ታደሰ አዲሱ ተቋምን አስመልክቶ በምክክሩ ላይ የሚቀርቡ ዋና ዋና ሰነዶችን ገልፃ አድርገዋል። የዴስክ ኃላፊዋ የተቋማዊ አደረጃጀት ፣ ህጋዊ ማዕቀፍና የፋይናንስ ምንጭ በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡
የቴክኒካል ስፔሻሊስት አማካሪ የሆኑት አቶ አበራ ተስፋዬ ተቆጣጣሪ ተቋሙ ራሱን ችሎ ወደ ሙሉ ትግበራ እስከሚገባ ድራስ በሽግግር ጊዜ የሚመራ የጋራ ትግበራ ተቆጣጣሪ ቡድን (Jiont Regulatory Implementation Team JRIT) በሚኒስቴሩ የበላይ አመራር መሰየሙን ገልጸዋል።
በሽግግሩ ጊዜ በጋራ ትግበራ ተቆጣጣሪ ቡድን በፍኖታ ካርታ እና በድርጊት መርሀ ግብር ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት ዘርዘር ያሉ ጉዳዮች አንስተው ለተሳታፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። አማካሪው አያይዘውም ቡድኑ ህጋዊ ማዕቀፍ እነንዲጸድቅ ማድረግና የተቆጣጣሪ የተቋማዊ አደረጃጀት ወደ መሬት መውረድ ፣ እና የፋይናንስ ምንጭ መለየት ፣ የሰው ኃይልና የቢሮ ቁሳቁሶችን ማሟላት በሽግግሩ ጊዜ የሚከናወኑ ሥራዎች መሆኑን ገልጸዋል።
የበጀት ምንጭ ከየት ያገኘል፣ የከተሞች የአገልግሎት ቦርድ እና በተቆጣጣሪ ቦርድ መካከል ያለው ልዩነት እና ከክልሎች ጋር የህግ ማዕቀፉ ቅንጅት እና ተፈፃሚነት በምን መልኩ ተግባራዊ ይሆናል የሚሉ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ቀርበው በአማካሪዎች እና የድህረ የውሃ ተቋማት ግንባታ ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ በአቶ ሃይማኖት በለጠ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የተቆጣጣሪ ተቋሙ አሁን የሚስተዋሉ የከተማ መጠጥ አቅርቦትና ሶኒቴሽን አገልግሎት ተግዳሮቶችን በመፍታት በሀገር ደረጃ ወጥነት ያለው የቁጥጥር እና የክትትል አሰራር በመፍጠር ቀልጣፋ እና ውጤታማ የከተሞች የውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን አገልግሎት ያሰፍናል ተብሎ ይጠበቃል።