በከተሞች እየተስተዋለ ያለውን ገንዘብ ያልተከፈለበት ውሃ አስተዳደር ችግርን በሚመለከት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

በከተሞች እየተስተዋለ ያለውን ገንዘብ ያልተከፈለበት ውሃ (Non-Revenue Water) አስተዳደር ችግርን በሚመለከት ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ጥቅምት 29/2015ዓ.ም (ውኢሚ) የኢትዮጵያ የከተሞች ውሃ ፌደሬሽን ከአፍሪካ የውሃ ማህበር ጋር በመተባበር በከተሞች እየተስተዋለ ያለውን ገንዘብ ያልተከፈለበት ውሃ (Non-Revenue Water) አስተዳደር ችግር ለመፍታት የሚያስችል ለውሃ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ለጥገናና አፕሬሽን እንዲሁም ለፋይናንስ ኃላፊዎች ለሶስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና በአዲስ አበባ አዚማን ሆቴል እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ስልጠናውን በይፋ የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ እንደገለጹት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዜጎችን በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ያለ መሆኑንና እስካሁን ባለው ሁኔታም ወደ 60 በመቶ አካባቢ ተደራሽ ለማድረግ መቻሉን ጠቁመው የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ የተሻለ አደረጃጀት በመፍጠርና ተቋማዊ አቅም በመገንባት ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚሰራ ጠቅሰው ህይወት የሆነውን የውሃ ሀብታችን ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን በመስራት እንደ አለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና ዩኒሴፍ እና ሌሎች የልማት አጋሮች ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ለመሆን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ አማካሪው አያይዘውም ገንዘብ ያልተከፈለበት ውሃ (Non-Revenue Water) ክስተትን ለመከላከል በርካታ መንገዶች እንዳሉና አስቸጋሪና ፈታኝ ጉዳዮች ቢኖሩም አሁንም ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንደሚገባ ገልጸው የአፍሪካ የውሃ ማህበር በጉዳዩ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለውን ስራ በማንኛውም ጊዜ እንደሚደግፉም አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ የአፍሪካ ውሃ ማህበር ተወካይ ዶ/ር ኢ/ር Simeon Kenfack, በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት የአፍሪካ የውሃ ማህበር ከተመሰረተ በርካታ ዓታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉ በኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች በመደገፍ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝና የስልጠናው ዋና አላማም ዘርፉ ላይ የሚታየውን ተግዳሮት ለማስተካከል ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጲያ የከተሞች ውሃ ፌደሬሽን ዋና ሴክሬታሪ የሆኑት አቶ ቡሽራ ሙሃመድ በአለም ላይ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የውሃ ኩባንያዎች በአሰራርና በአስተዳደር ስርዓታቸው ላይ ከባድ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸውና አንዱና ዋነኛው ደግሞ ከውሃ ብክነት ጋር በተያያዘ በኔትወርክ፣ ብልሽት፣ በማጭበርበር፣ በሂሰብ አከፋፈል ችግርና በመለኪያ መሳሪያ ምክንያት ሲሆን ይህ ችግር በአፍሪካ አገራት ኢትዮጲያን ጨምሮ የበዛ ሲሆን ችገሩ የታለመውን ህዝብን የማገልገል አቅሙን በመቀነስ የውሃ ተቋማትን የፋይናንስ አዋጭነት በእጅጉ የሚጎዳ ነው ብለዋል፡፡ ስልጠናው በዋናነት የውሃ ኩባንያ ተቋማዊ፣ ስትራቴጃዊ፣ ቴክኒካልና የንግድ ትንተና ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰጥ ሲሆን አላማውም ያልተከፈለ ውሃ ሁሉንም አካላዊ ፣ንግድና ማህበራዊ ጉዳዮችን በመረዳት ፣ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ማከፋፈያ ስርዓትን ኦዲት ለማድረግ ፣ የመጠጥ ውሃ ኔትወርክን መዘርጋትና በመጠጥ ውሃ ስርዓት ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን መቆጣጠር እንዲቻልና የሚንጠባጠቡ ንጹህ መጠጥ ዉሃዎችን ለማወቅ በሚያስችል መልኩ የተቀረጸ ነው፡፡

Share this Post