የአለም የእጅ መታጠብ እና የመፀዳጃ ቤት ቀን ተከበረ።

የአለም የእጅ መታጠብ እና የመፀዳጃ ቤት ቀን ተከበረ። ህዳር 13/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የአለም የእጅ መታጠብ እና የመፀዳጃ ቤት ቀን በአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተከበረ። '’ንፁህ እጆች ለጤናችን ዋስትና ናቸው!’’ በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ ለ16ኛ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ15ኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የእጅ መታጠብ ቀን እና ''መፀዳጃ ቤትን በንፅህና መያዝ እና መጠቀም ዘመናዊነት ነው!'’ በሚል መሪ ቃል በአለም አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የመፀዳጃ ቤት ቀን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጤናና ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ተከበረ። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ የሳኒቴሽን አገልግሎት እና የንፅህና አጠባበቅ ለሰው ልጅ መሰረታዊ መሆናቸውን ገልፀው፤ ሳንቴሽን የመፀዳጃ ቤት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የጤናና የልማት ጉዳይ ነው ብለዋል። ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ከከተማና ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት ባለመከተላችን የጤና፣ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያቤታችን በተሰጠው ሀላፊነት መሰረት ዘርፈ ብዙ የሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ስራዎችን የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል ብልዋል፡፡ መፀዳጃ ቤት የተሟላ የእጅ መታጠቢያ ሊኖረውና በአግባቡ የእጅ መታጠብ ባህልን ማዳበር የሚገባ ነው ያሉት ክቡር ሚኒሰቴር ዴኤታው የሳኒቴሽን ስራ በባህሪው ቅንጅት ስለሚፈልግ በየደረጃው ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የአቅም ግንባታ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በቀጣይነት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በዋን ዋሽ ፕሮግራም በሳኒቴሽን ዙሪያ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን አንስተው የበአሉ መከበር ዋናው አላማ የፅዱ ኢትዮጵያ 2030 መርሃግብር በሳኒቴሽንና ሀይጅን ዙሪያ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ እና የውሃ፣ የሳኒቴሽንና የሀይጅን አገልግሎት እንዲሁም የጤና ሁኔታን በዘላቂነት ለማሻሻል ያለመ ነው ብለዋል። በመደረኩም በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ Mr. Mariko Kagoshima፣ የአለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አመራሮችና ሰራተኞች፣ የልማት አጋር ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

Share this Post