በተዘጋጁ የጂኦሎጂና የሃይድሮጂኦሎጂ ካርታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደረገ፡፡

በተዘጋጁ የጂኦሎጂና የሃይድሮጂኦሎጂ ካርታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደረገ፡፡ ጥቅምት /2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከቼክ ሪፐብሊክ የልማት አጋር ጋር በጋራ በሲዳማ ክልልና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌድዮና ጋሞ ዞን ላይ በተዘጋጀው የጂኦሎጂና የሃይድሮጂኦሎጂ ካርታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ፡፡ መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ኢትዮጵያ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዳላት አንስተው ሀይድሮጂኦሎጂ ለኢትዮጵያ ወሳኝ በመሆኑ ጥናቱ በውሃ እጥረትና በውሃ ጥራት ላይ ለምናደርገው ጥረት ላይ ያለብንን ጫና ይቀንሳል ብለዋል። በካርታው ዝግጅት ላይ የተሳተፉትን የቼክ የፐብሊክንና የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን እያመሰገንኩ በሂደቱም ብዙ ትምህርት የወሰድንበት ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ስርዓት ላይ ተጨማሪ ግብአት ያገኘንበት ነው ብለዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒሰትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ ኢትዮጵያ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት ያላት ስትሆን የከርሰ ምድር የውሃ ሀብት የት ቦታ፣ ምን ያህል መጠንና ጥራት እንዳለ ለማወቅ የጂኦሎጂውን ሁኔታ ማጥናት ወሳኝ በመሆኑ ከጥናቱ በኋላ የሚተነተኑ፤ የውሃ መጠኑን የሚለዩ የሃይድሮ ጂኦሎጂውን የውሃ መጠን ተለይቶ እዚህ ቦታ በዚህን ያህል መጠን የሚለውን ለመለየት የሚያስችል ጥናት በቼክ ሪፐብሊክ ጋር በጋራ የሚሰራ ሲሆን የጂኦሎጂካል ጥናት የአዲስ አበባ፣ የአርባ ምንጭና ሌሎት ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ በማሳተፍ በናሙና ደረጃ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲዮና ጋሞ ዞን አካባቢ የሚሰራ ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት ተጠንተው የነበሩ የጂኦሎጂ ካርታዎችን መሰረት በማድረግ አጠቃላይ የሀገሪቱን የጂኦሎጂ ካርታ በማዘጋጀት ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሀይድሮ ጂኦሎጂ ካርታ ውሃ ሊሰጡ የሚችሉ የድንጋይ/አለት አይነቶች፣ መጠናቸውና ጥራታቸው ምን ያህል ነው የሚለውን ባለፉት አራት አመታት በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ጥናቱ ተጠናቆ ከመታተሙ በፊት ከዚሁ ሙያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ከማዕድን ሚኒስቴርና ከሶስቱ ወረዳዎቾ ተሳትፈው በውይይት ዳብሮና ግብዓት ተወስዶ በሚቀጥለው አመት ረቂቁን ካርታ ለማሳተም የቀሩ ነገሮች ካሉ ለማየት የሚያስችል መድረክ መሆኑን ገልፀዋል። ከጥናቱ አቅራቢዎች መካከል ከቼክ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ባለሙያ ዶ/ር ለታ አለማየሁ በበኩላቸው የከርሰምድር ውሃ ለኛ ሀገር ወሳኝ በመሆኑ ከሌሎች የውሃ ሀብቶች በቀላሉ ሊለማ የሚችል በመሆኑ ብዙ ጥናትና ቅድመ ዝግጅት የሚፈልግ በመሆኑ ያሉብንን ተግዳሮቶች ለማጥበብ ያግዛል ብለዋል። በመድረኩም የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ፣ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂና ከአዋሳ ዩኒቨርስቲ፣ ከማዕድንና ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት፣ ከደችና ከቼክ ኢምባሲ እና ከተለያዩ ካምፓኒዎች እንዲሁም ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀረበው ሰነድ ላይ ሰፊ ውይይት ተካሄዷል።

Share this Post