የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ ።

የላይኛው አዋሽ ተፋሰስ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ ።

ሰኔ 24/ 2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ.) የላይኛው የአዋሽ ተፋሰስ ቅድመ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ ።

በላይኛው አዋሽ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የግንባታ ሥራውን ያስጀመሩት የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በጎርፍ ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ስጋቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ከአለም ባንክ በተገኘ የ300 ሚልዮን ዶላር ድጋፍ የኢትዮጵያ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ተቀርጾ ዝግጅት ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸው፤ በአየር ንብረት ለውጥ ትንበያ መሠረት ከመደበኛና ከመደበኛ በላይ በክረምት ዝናብ ምክንያት ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋ መነሻ በማድረግ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ሊሰሩ የሚችሉ ተግባራትን ከባንኩ ጋር በመለየት በልዩ ሁኔታ በላይኛው፣ በመካከለኛው እና በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በዚህ የአስቸኳይ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ በላይኛው አዋሽ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትና ከ27 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከአደጋ ጉዳት መቀነስ የሚያስችል ሥራ ይፈፀማል ብለዋል ።

ክቡር ሚኒስትር ድኤታው የኢትዮጵያ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲቲዩት ተቋማት የጎርፍ አደጋ ስጋት ቅነሳ ያላቸውን ተቋማዊ አቅም መገንባት እንደሚጨምር፤ እንዲሁም በውና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኩል የዳይክ ስራ፣ የወንዝ አመራር እና ሌሎች ስራዎችን በሰባት ቤዚኖች መተግበርን እንደሚያካትት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከተማ በበኩላቸው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተጀመረው ቅድመ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ የጎርፍ አደጋ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ ከፍተኛ የጎርፍ ክስተቶች በሚስተዋልባቸው ቤዚኖች ውስጥ፤ ማለትም በአዋሽ ፣ በስምጥ ሸለቆ እና በኦሞ ጊቤ ቤዚኖች የቅድመ ጎርፍ መከላከል የግንባታ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የላይኛው የአዋሽ ተፋሰስ ቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራ በኦሮሚያ ክልል በ7 ወረዳዎች (ኢሉ፣ ኤጀሬ፣ ኤጀርሳ፣ ላፎ፣ ዳዋ፣ ሰበታ ሀዋስ፣ ሊበን እና ቦራ) የሚያካትት ሲሆን፤ የፕሮጀክቱ አላማ የጎርፍ አደጋው በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት አደጋ ማስቀረት የሚያስችሉ የቅድመ ጎርፍ መከላከል ሥራዎች ማከናወንን እንደሚጨምር አውስተዋል።

በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ነሲቡ ያሲን፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ የኢሉ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ተስፋ የተገኙ ሲሆን፤ አስተዳዳሪው ፕሮጀክቱ መጀመሩ የህብረተሰቡን የጎርፍ አደጋ ስጋት እንደሚቀርፍ እምነታቸውን ገልፀዋል።

በመጨረሻም የኢሉ ወረዳ አስተዳደር፣ አልሰን ፍሮምሳ የስራ ተቋራጭ እና ዲ.ኤች አማካሪ ድርጅት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት እና የቦታ ርክክብ ተፈራርመዋል።

Share this Post